“የዲጅታላይዝሽን ሥራ የዜጎቻችንን እንግልት፣ ወጭ እና ጊዜ ትርጉም ባለዉ ሁኔታ የቀነሰ ነው” ዓለምአንተ አግደው

5

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን ፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ በመሰረታዊነት ለማሻሻል የአጭር ጊዜ ዕቅድ በማዘጋጀት እየሠራ ይገኛል።

በየደረጃው የሚተገበሩ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን እቅዶች እውን ለማድረግ ከመደበኛው የተቋሙ ዓመታዊ እቅድ በተጨማሪ በልዩ ትኩረት የሚከናወኑ የመቶ ቀናት እቅዶችን በማዘጋጀት ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አስታውቋል። የተከናወኑ ዋና ዋና አፈጻጸሞችን መነሻ በማድረግም የቀጣዮቹ መቶ ቀናት እቅዶች ተቀምጠዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አለምአንተ አግደው፣ በመጀመሪያው መቶ ቀናት የታቀዱ እና የተከናወኑ ሥራዎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የክልሉን ፍርድ ቤቶች ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ፣ ተገማች፣ ተደራሽ እና ወጭ ቆጣቢ በማድረግ የክልሉን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ በመሰረታዊነት ለማሻሻል ለያዘው ርዕይ ተፈጻሚነት ከፍተኛ ድርሻ እንደነበራቸው አስገንዝበዋል።

በተለይም የተጀመረዉ የዲጅታላይዝሽን ሥራ የዜጎቻችንን እንግልት ፣ወጭ እና ጊዜ ትርጉም ባለዉ ሁኔታ የቀነሰ በመሆኑ ሁሉም የተቋሙ ባልደረቦች ሊኮሩበት የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተማከለ የዳኝነት ኮምፕሌክስ ግንባታ የማስጀመር ሂደት፣ የባሕል ፍርድ ቤቶችን በተሟላ ሁኔታ መደገፍ ፣ የዘመናዊ እና ዲጅታል ፍርድ ቤቶች በክልሉ እውን መሆን፣ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን በመሰረታዊነት ማሻሻል፣ የዳኞችን፣ የሰራተኞችን አቅም ማጎልበት፣ በሥነ-ምግባር ረገድ የሚነሱ ጉዳዮችን ማረምና ዘላቂ መፍትሄ እየሰጡ መሄድ፣ የተቋሙን የመዋቅር እና የሕግ ማሻሻያ ሥራዎች ማጠናቀቅ ዋናዎቹ የቀጣይ የትኩረት መስኮች መሆናቸውን ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል።

የተቋሙ የተለያዩ ክፍሎች ያቀረቧቸው እቅዶች ለተቋሙ ርዕይ መሳካት የጎላ ድርሻ እንዳላቸው የገለጹት የትራንስፎርሜሽን ቡድኑ አባላት በበኩላቸው፣ እቅዶቹ በልዩ ትኩረት ሊተገበሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፍቼ ጨምበላላ በዓል ባሕላዊ እሴቱን ጠብቆ እና ሲዳማን አድምቆ ተጠናቅቋል።
Next articleበፍቅር እና በአንድነት በመቆም የሀገርን ሰላም እና ልማት ማስቀጠል ይገባል።