የፍቼ ጨምበላላ በዓል ባሕላዊ እሴቱን ጠብቆ እና ሲዳማን አድምቆ ተጠናቅቋል።

3

 

አዲስ አበባ፡ መጋቢት 06/2018 ዓ.ም(አሚኮ) የሲዳማ ፍቼ ጨምበላላ በዓል ባሕላዊ እሴቱን ጠብቆ ተከብሮ መጠናቀቁን አስመልክቶ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ እና የባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የሲዳማ ክልል የዘመን መለወጫ ፍቼ ጫምባላላ የሲዳማ አባቶች መጋቢት 5 እና 6 ይከበር ባሉት መሠረት ሰፊ ዝግጅት ተደርጎ በደማቅ ሁኔታ መከበሩን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ወሰንየለህ ስምዖን በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል።

በበዓሉ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች መገኘታቸውንም ገልጸዋል።

ከዋዜማው ጀምሮ ሁሉም የበዓል ዝግጅቶች በታቀደላቸው መልኩ ተዘጋጅተው እንደ አዲስ በተዋበችው ሀዋሳ መከበር ችሏል ብለዋል።

በዓሉ የሰላም እና የወንድማማችነት መኾኑን በግልጽ ያሳዬ ኾኖ ማለፉን ኀላፊው ተናግረዋል።

ለዚህም የሚዲያ አካላት ላደረጉት የዘገባ ሽፋን፣ ለፀጥታ አካላት እና ለሀዋሳ ከተማ ሕዝብ እንዲሁም የድርሻቸውን ለተወጡ ሁሉ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።

የባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊው ጃጎ አገኘሁ በበኩላቸው በዓሉ ባሕላዊ እሴቱን፣ የዓለም ቅርስነቱን እና ኅብረ ብሔራዊነቱን ጠብቆ መከበሩን ተናግረዋል።

የሲዳማ ሕዝብ እና የሀዋሳ ነዋሪም ዳኤ ቡሹ ብሎ ባሕሉን ጠብቆ እንግዶቹን ተቀብሎ አስተናግዷል ብለዋል።

የመገናኛ ብዙኀን አካላት የበዓሉን እሴቶች ለመላው ኢትዮጵያዊ እና ዓለማቀፍ ማኅበረሰብ በማስተዋወቅ ረገድ ለነበራቸው አስተዋጽኦ አመሥግነዋል።

በዓሉ በተለይ ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም ዕድገት እና ለቱሪዝም ፍሰቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጦርነት በቃኝ በማለት ለሰላም ደጀን መኾን ይገባል።