ጦርነት በቃኝ በማለት ለሰላም ደጀን መኾን ይገባል።

2

 

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ከተማ “ለሰላም ዘብ እንቆማለን ለልማት አርበኛ እንኾናለን” በሚል መሪ መልእክት ከከተማው መንግሥት ልማት ድርጅቶች ሠራተኞች ጋር ውይይት ተካሄዷል።

በመድረኩም እንደ ሀገርን እና እንደ ክልል ያሉ ውስጣዊ እና ውጫዊ ተግዳሮቶችን የሚዳስስ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።
በወልዲያ ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋየ ገብሬ በሚፈጠሩ ችግሮች ከፍተኛ ጉዳት እያስተናገዱ የሚገኙት የልማት ድርጅቶች እንደኾኑ ገልጸው ለዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ሠራተኞች ከመንግሥት ጋር በጋራ እንዲሠሩ ጠይቀዋል።

የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ የኢትዮጵያን እድገት እውን ለማድረግ የባሕር በር ያስፈልጋታል፤ ይህን ሀገራዊ አጀንዳ ለማስጣል ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጥረት እያደረጉ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አባቶቻችን ትናንት አንገዛም ብለው በመታገል ነጻ ሀገር አስረክበውናል፤ ሁላችንም አንድ በምታደርገን የጋራ እናታችን የመጣውን ታሪካዊ ጠላት ለመቀልበስ ህያው የኾነ መስዕዋትነት እንደ አባቶቻችን መክፈል ይገባናል ብለዋል።

ድህነት፣ ጉስቁልና እና ሥራ አጥነትን ለማስወገድ እና ከተማዋን ስማርት ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ ነው ያሉት ከንቲባው ይህን የልማት ሥራ ለማስቀጠልም ጦርነት በቃኝ በማለት ለሰላም ደጀን መኾን ይገባል ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ማዕድን ቢሮ ምክትል ኀላፊ ታምራት ደምሴ የልማት ድርጅት ሠራተኞች ወቅታዊ ሀገራዊ፣ ክልላዊ እና አካባቢያዊ የሰላምና የልማት ሁኔታዎችን በመረዳት ለዘላቂ ሰላም መስፈን የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ያለ ሰላም ልማት አይታሰብም ያሉት ተሳታፊዎቹ ምንም እንኳን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ልማቶች እየተሠሩ ቢሆንም የተሠሩ ልማቶችን ዘላቂነት ለማረጋገጥ የማኅበረሰቡን አመለካከት መቀየር ላይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት።

ቀይ ባሕር ታሪካዊ ሀብታችን ነው፤ ለኛ ይገባናል፤ ይኼን አመለካከት በሁሉም ማኅበረሰብ ለማስረጽ ተከታታይ የኾነ ውይይት በተቋማት ሊያካሂዱ ይገባል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የፊቼ ጫምባላላ በዓል ኅብረ ብሔራዊነትን እያጎላ ያለ በዓል ነው” አቶ አገኘሁ ተሻገር