
አዲስ አበባ: መጋቢት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በዓል በሀዋሳ ሶሬሳ ጉዱ ማሌ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት ምክንያት ሕይወታቸውን ባጡ ወገኖች የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።
የሲዳማ ሕዝብ ራሱን በራሱ ማሥተዳደር ከጀመረ ጀምሮ “የፊቼ ጫምባላላ በዓል ኅብረ ብሔራዊነትን እያጎላ ይገኛል” ብለዋል። ይህ ብቻ ሳይኾን ራሱን በራሱ እያሥተዳደረ ልማት እና ሰላምን እያረጋገጠ መኾኑንም አንስተዋል።
ሲዳማ የራሱ አኩሪ ባሕል እና ማንነት ያለው ነው ያሉት አፈጉባኤው ፊቼ ጫምባላላ የአብሮነት፣ የይቅርታ እና የእርቅ በዓል ኾኖ የዘለቀ ነው ብለዋል።
የዘንድሮው በዓል ከመሠረተ ልማት እና ከዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጋር በሌሎች የልማት ሥራዎች እና ሁነቶች ታጅቦ መከበሩ የተለዬ ያደርገዋል ነው ያሉት።
በመጭው ምርጫም ሕዝቡ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ዋና አፈ ጉባኤው አሳስበዋል።
ራስን ከወቅታዊ ሀገራዊ እና ዓለማቀፋዊ ሁኔታዎች ጋር በማዋሃድ ለሰላም እና ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
