በዓለ ደብረ ዘይት የምጽዓት መታሰቢያ

3

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት ደብረ ዘይት እየተባለ ይጠራል። ይህ በዓል ምስጢራት የሚነገሩበት፤ የመጨረሻው ዘመን የሚታሰብበት፤ ምዕምናን ለአምላካቸው ምስጋና እና ምልጃ የሚያቀርቡበት ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የቤተክርስቲያን ታሪክ መምህር መምህር ይትባረክ ደምለው ደብረ ዘይት የቦታ ስም ነው፤ ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ አቅጣጫ የሚገኝ ከፍተኛ ቦታ ነው ብለዋል። ደብር ማለት በግዕዝ ተራራ ማለት ሲኾን ዘይት ደግሞ ወይራ ማለት እንደኾነ ተናግረዋል። ደብረ ዘይት ማለት በወይራ ዛፍ የተሸፈነ ተራራ ማለት እንደኾነ ነው መምህሩ የገለጹት።

በዚህ ተራራ ኢየሱስ ክርስቶስ ምስጢር የገለጠበት፤ ስለ ዓለም ፍጻሜ የመጀመሪያ ምልክቶች ለደቀመዛሙርቱ የተናገረበት ነው ይላሉ። ምዕመናን ስለሚገጥማቸው ፈተና፣ ስለ ዓለም ፍጻሜ እና ስለ ዳግም ምጽዓት አስተምሯል ነው ያሉት።

ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የዳግም ምጽዓቱን ምልክቶች ሲነግራቸውም ሐሰተኛ ክርስቶሶች ይነሳሉ፤ ጦርነት፣ ርሀብ፣ የክርስቲያኖች መከራ መሰማት፣ የሐሰተኞች ነቢያት መበራከት፣ የፍቅር መጥፋት ይኖራል። ይህም በኾነ ጊዜ ክርስቶስ እንደሚመጣ እና ጊዜው እንደተቃረበ የሚያሳይ ምልክት መኾኑን የሚያሳይ ነው ይላሉ።

የሰው ልጅ ፍቅር፣ ሰላም እና ትዕግስት መላበስ ካልቻለ በመጨረሻ በፈጣሪው ፊት ለመቅረብ እንደሚቸግር እና የክርስቶስ ማደረያ ሊኾን እንደማይቻል ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሯል ብለዋል። የሰው ልጅ ልቦና በፍቅር፣ በቅንነት፣ በሰላም፣ በአንድነት እና በመረዳዳት የተመላ መኾን አለበት ነው የሚሉት።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም ምጽዓቱን አስመልክቶ የሰጠውን ትምህርት በማስታወስ ታስተምራለች ብለዋል።

ምዕመናንም በዚሁ ዕለት አምላካቸውን አብዘተው ያስባሉ፤ ወደ አምላካቸው ይቀርባሉ፤ ንስሐም ይገባሉ፤ ይጸልያሉ፤ ይማጸናሉ ነው ያሉት መምህሩ።

ምዕምናን ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን እና ትግስትን በማዘውተር የክርስቶስን አስተምህሮ አርዓያነት መከተል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለዉ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሲዳማ የዘመን መለወጫ በዓል ፍቼ ጫምባላላ እየተከበረ ነው።
Next article“ጫምባላላ ለሰላም የሚጸለይበት፣ ቁርሾ እና ጥላቻ የሚወገድበት ሥርዓት ነው” አቶ ደስታ ሌዳሞ