
አዲስ አበባ: መጋቢት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ የፊቼ ጫምባላላ በዓል ዋዜማ “የፊጣራ” ሥነ ሥርዓት በሀዋሳ ከተማ እየተከበረ ይገኛል።
ሲዳማ የራሱ ባሕል፣ ቋንቋ፣ ማንነት፣ የጊዜ አቆጣጠር እና አስደማሚ ማንነት ያለው ድንቅ ሕዝብ ነው ያሉት የሲዳማ ክልል ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ ጀጎ አገኘሁ ናቸው።
የፊቼ ጫምባላላ በዓል በዩኔስኮ ከተመዘገበ ዘንድሮ 11ኛ ዓመቱን መያዙን ገልጸዋል። ለዚህም አስተዋጽኦ ለነበራቸው አካላት ኀላፊው ምስጋና አቅርበዋል።
በዓሉ ሲከበር እሴቶችን በተከተለ መልኩ መኾን እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።
እንኳን የዓለም ቅርስ ለኾነው የፊቼ ጫምባላላ በዓል አደረሳችሁ ያሉት ደግሞ የሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ ናቸው። የሲዳማ ሕዝብ ያለውን ባሕል እና እሴት በመጠበቅ ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅበታል ብለዋል።
“ፊቼ ጫምባላላን ስናከብር የበዓሉ እሴት የኾነውን አንድነት እና ኅብረታችንን ይበልጥ በማጠናከር ሊኾን ይገባል” ነው ያሉት።
የሲዳማ ሕዝብ አዲስ ዘመን ለማክበር በቅተናል ብለዋል። በዓሉ የበጎነት፣ የደስታ፣ ያዘነው የሚጽናናበት፣ የተበደለ የሚካስበት፣ ያጣ የሚያገኝበት፣ በአፊኒ የሽምግልና ሥርዓት የተጣላ የሚታረቅበት እና የአቃፊነት በመኾኑ አዲሱን ዓመት እነዚህን እሴቶች በመጠበቅ መሻገር ይገባል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
