ውጤታማ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

3

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዙር 13ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።

የከተማ አሥተዳደሩ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ እናትነሽ ዋለ በከተማዋ ሰፋፊ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል። ለአብነትም የኮሪደር ልማት፣ የስማርት ሲቲ ግንባታ እና የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

የስማርት ሲቲ አፈጻጸምን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ሕጋዊ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለት በአደረጃጀት እና በመዋቅር ተደግፎ ሊሠራበት እንደሚገባም አሳስበዋል።

መልካም ተግባራት እንዲቀጥሉ እና ድክመቶች እንዲስተካከሉ ምክር ቤቱ የተጠናከረ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በከተማዋ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት እና ማነቆዎችን በመፍታት ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

ከተማዋ ከቱሪዝም ዘርፉ በሚገባት ልክ ተጠቃሚ ለመኾን ጠንካራ የትውውቅ ሥራዎች እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል። ስማርት ሲቲ አሠራርን በተሟላ መንገድ በመተግበር ዘመናዊ የዲጂታላይዜሽን ተግባራት ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሠራል ነው ያሉት።

የጎንደር ከተማ የጸጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱንም ጠቁመዋል። አስተማማኝ ሰላምን ለማረጋገጥም የጸጥታ አካላት፣ መሪዎች እና መላው ሕዝብ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።

የከተማው ሕዝብ ቁጭቱን የተወጣበት የኮሪደር ልማትም በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ እንደሚገኝም አብራርተዋል። መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ከፍ ባለ ደረጃ ግንባታው እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የምክር ቤቱ አባል የኾኑት ሞገስ መኮነን ጉባኤው የከተማዋን የኢቨስትመንት ማስፋፋት፣ ስማርት ሲቲ ፕሮጀክት አተገባበር እና በከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ስለመኾኑ አስተያየታቸውን ለአሚኮ ሰጥተዋል።

ምክር ቤቱ የተለያዩ የከተማ አሥተዳደሩ የተቋማት አሥፈጻሚዎችን ሹመትም አጽድቋል።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሐሰተኛ መረጃ ስርጭት የሰላም ግንባታ ሥራዎችን ያደናቅፋል።
Next articleየዓድዋ ድልን እና የእቴጌ ጣይቱን ግለ ታሪክን የሚያትት መጽሐፍ ተመረቀ።