ፍቅር እና ሰላም የሚሰበክበት ፊቼ ጫምባላላ!

7

 

አዲስ አበባ: መጋቢት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፊቼ ጫምባላላ ዋዜማ በሲምፖዚየም እና በሌሎች ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።

ፊቼ ጫምባላላ በሲዳማ ሕዝብ ዘንድ በድምቀት የሚከበር ታላቅ በዓል ነው። ይህም የሲዳማ ሕዝብ የአዲስ ዓመት በዓል መግቢያን እና ዘመን መለወጫ የሚበሰርበትም ነው።

በፊቼ ጫምባላላ ሕዝቡ በደስታ ይሠባሠባል፤ ባሕላዊ ሥነ ሥርዓቶችን ይፈጽማል፤ አዲስ ዓመትን በተስፋ እና በደስታም ይቀበላል።

የሲዳማን ሕዝብ ባሕል፣ ታሪክ እና አንድነትን የሚያሳይ ድንቅ እና ክብር ያለው በዓልም ነው ፊቼ ጫምባላላ።

“ፊቼ” የአዲስ ዓመት መግቢያን ማብሰሪያ ዋዜማ ነው። በዛሬው ዕለትም “የፊጣራ” ምሽት የሚከበርበት ሥርርዓት ነው።

ዛሬ ቡርሳሜ በእርጎ በአባቶች ተባርኮ እና ያለልዩነት ለቀጣዩ ዓመት በሰላም አድርሰን ተብሎ ተመርቆ የአንድነት እና የመተሳሰብ መገለጫ በኾነው በሻፌታ ሙሉው ወይም “ዎማ” ቀርቦ የመቋደስ ሥርዓቱ በሰፊው የሚካሄድበት ዕለት ነው። ነገ ደግሞ በሶሬሳ ጉዱማሌ ጫምባላላ የሲዳማ ዘመን መለወጫ ይከበራል።

ፊቼ ጫምባላላ ለማኅበረሰቡ አንድነት ትልቅ ሚና አለው። ሰዎች ከተለያዩ ቦታዎች ተመልሰው ከቤተሰብ ጋር ይገናኛሉ። ይህ በዓል ፍቅርን፣ ሰላምን እና መተባበርን ያጠናክራል።

የፊቼ ጫምባላላ በዓል በዓለም ቅርስነት በዩኔስኮ ከተመዘገበም እነኾ 10 ዓመታትን አስቆጥሯል።

በበዓሉ የሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የበዓሉን እሴት የሚመለከት ሲምፖዚየም እየተከናወነም ይገኛል።

ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ተጎጅዎች የሚደረገው ድጋፍ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጹ።
Next articleየሐሰተኛ መረጃ ስርጭት የሰላም ግንባታ ሥራዎችን ያደናቅፋል።