የክልሉ መንግሥት የዋግኽምራ ሕዝብ የልማት ጥያቄዎችን እየመለሰ መኾኑን ነዋሪዎች ተናገሩ።

9

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በወቅታዊ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ክልሉ የዋግኽምራን ሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ እያደረገ ያለው ጥረት የሚመሰገን መኾኑን በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ለሰቆጣ ጠቅላላ ሆስፒታል የሲቲ ስካን ማሽን እንዲሟላ፤ የተጀመሩ መንገዶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ፤ የዛታ ወፍላ እና ኮረም የወሰን እና የማንነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በትኩረት ሊሠራ ይገባልም ብለዋል። ሰላምን ለማጽናት እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት እሸቱ ለሰቆጣ ከተማ አጠቃላይ ሆስፒታል ማስፋፊያ ግንባታ መደረጉ እና በሰሜኑ ጦርነት ተቋርጦ የነበረው የአስፋልት ግንባታ መጀመር፤ በ152 ሚሊዮን ብር የክልል ድጋፍ የገብያ ማዕከል ግንባታ መጀመር እና ለውቅር መስቀለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የቅርስ እድሳት በማድረግ የክልሉ መንግሥት የሕዝብን ጥያቄ መልሷል ብለዋል።

የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ ሹመት ጥላሁን በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የጤና፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃ እና የማዕድን ሃብትን ለማልማት የክልሉ መንግሥት ልዩ ድጋፍ በማድረግ እየሠራ ነው ብለዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሐ ደሳለኝ የሰላም እጦቱ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በፍጥነት እንዳይጠናቀቁ እንቅፋት መኾኑን ገልጸዋል።

ክልሉ በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾኖም የማኅበረሰቡን ጥያቄ ለመመለስ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የወሰን ጥያቄዎች በዘላቂነት ምላሽ እንዲያገኙ ክልሉ በትኩረት እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) ልዩነትን በመተው አንድነትን ማጠናከር ላይ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። የሥራ ኀላፊዎች በሚችሉት አቅም ሁሉ የማኅበረሰቡን የልማት ጥያቄዎች እንዲመልሱም አሳስበዋል።

ጫካ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ነዋሪዎች የበኩላችሁን ድርሻ ልትወጡ ይገባል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የውስጥ የጥፋት ኃይሎች እና የውጭ ባንዳዎች የዋግ ሕዝብ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ትሩፋቶችን እንዳያገኝ እንቅፋት ፈጥረዋል ብለዋል።

ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር፤ ከከፋፋይ ትርክት እና ተግባር መራቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የክልሉ መንግሥት 9 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ የልማት ሥራዎችን በብሔረሰብ አሥተዳደሩ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

ሲቲ ስካን ማሽን ለሆስፒታሎች ለማዳረስ ግዥ ላይ መኾኑንም ተናግረዋል። የመንገድ መሠረተ ልማቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደሚሠራም አንስተዋል።

ቀጣይ የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊ፤ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ማኅበረሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም መልእክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ወደ አርባምንጭ አቅንተዋል።
Next articleለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ተጎጅዎች የሚደረገው ድጋፍ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጹ።