አሚኮ ከአልማኮን ሕንጻ ተቋራጭ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።

9

 

ባሕርዳር፡ መጋቢት 05/2018ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከአልማኮን ሕንጻ ተቋራጭ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ እና የአልማኮን ሥራ አሥፈጻሚ ሰጥቷል ደሳለኝ ናቸው።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ አሚኮ የውጭ ሀገር ቋንቋዎችን ጨምሮ በብዙ ቋንቋዎች በሁሉም የሚዲያ አማራጮች አገልግሎት የሚሰጥ የሚዲያ ተቋም መኾኑን ተናግረዋል።

አሚኮ ባለቤቱ የአማራ ክልል ሕዝብ እና መንግሥት ቢኾንም ለመላው ኢትዮጵያ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ነው የገለጹት። አልማኮን ደግሞ የአገልግሎት ጥራቱን፣ ብቃቱን እና ውጤታማነቱን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያደርስ ተቋም መምረጡን ነው የጠቀሱት።

ቀደም ሲል አሚኮ ከአልማኮን ጋር ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን የተናገሩት ዋና ሥራ አሥፈጻሚው የተጀመረው ሥራ ብዙ ሂደት እና መግባባትን አልፎ አሁን ላይ መድረሱን አንስተዋል።

የተጀመሩ ሥራዎች የበለጠ ውጤታማ መኾን እንዲችሉም ተቋማቱ በጋራ መሥራትን ያጠናክራሉ ነው ያሉት።

በአልማ ውስጥ የሚገኘው አልማኮንም የበለጠ ሲያድግ እና ሲያተርፍ ለክልሉ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች አቅም እና አጋዥ እንደሚኾንም ተናግረዋል።

በቀጣይም ስምምነት ከተደረገባቸው የግንኙነት ማዕቀፎች ውጭ አሚኮ አገልግሎት ለመስጠት በሕግ የተሠጠውን ሥልጣን መሠረት አድርጎ በዘገባ እና በሌሎች አማራጮች ለአልማኮን የሚያደርገውን ድጋፋ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የአልማኮን ሥራ አሥፈጻሚ ሰጥቷል ደሳለኝ ደግሞ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና አልማኮን ሕንጻ ኮንስትራክሽን ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የብራንድ ትውውቅ እና ዘላቂነት ያለው የተግባቦት ሥራ ለመሥራት የጋራ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ተናግረዋል።

አልማኮን በአማራ ልማት ማኅበር አማካኝነት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲሠራ የተቋቋመ የገቢ ማስገኛ ተቋም መኾኑንም ገልጸዋል።

ባለፋት 12 ዓመታት አልማኮን ብዙ ሥራዎችን መሥራቱንም አንስተዋል። በተለይም ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ራሱን ሪፎርም በማድረግ ከኮንስትራክሽን ዘርፉ በተጨማሪ ሌሎች አዳዲስ የአገልግሎት ዘርፎችን ይዞ መምጣቱን ነው የጠቀሱት።

ከእነዚህም ውስጥ የቤት ልማት፣ የግንባታ ምርት እና አቅርቦት ዘርፍ ላይ በሰፊው ገብቶ እየሠራ እንደሚገኝም ነው የገለጹት።

እንደ ተቋም ራስን የማስተዋወቅ ክፍተት ነበረብን ያሉት ሥራ አሥፈጻሚው ይህንን ክፍተት ለመሙላት ከለውጥ ሥራዎች ጋር ተያይዞ የተሠሩ ሥራዎችን ለደንበኞቹ እና ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ አልማኮን ይፈልጋል ብለዋል።

ይህን ሥራ ለመሥራት ደግሞ የክልሉ ትልቅ ሀብት ከኾነውና ሰፊ ተደራሽነት ካለው አሚኮ ጋር በዘላቂነት አብሮ ለመሥራት በመስማማታቸው ደስተኛ እንደኾኑ ገልጸዋል።

ለአንድ ኹነት ብቻ ሳይኾን በዘላቂነት ረዘም ላለ ጊዜ ከአሚኮ ጋር አልማኮን የመሥራት እና አብሮ የማደግ ፍላጎት አለው ብለዋል።

በቀጣይ ከሚዲያ ሥራዎች ባሻገር የጥናት እና የምርምር ሥራዎች፣ በማኅበረሰብ አገልግሎቶች እና በሚያገናኟቸው በሌሎች ሥራዎች ዙሪያ በስፋት እንደሚሠራ አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኪነ ጥበብ ኢትዮጵያዊነትን ለማጽናት እና ለማነጽ ሚናው ከፍተኛ ነው።
Next articleለጥንቃቄ፦ በድምጽ ጥሪ አማካኝነት የሚፈጸም የሳይበር ጥቃት፦