
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 04/2018 ዓ.ም(አሚኮ) በኢትዮጵያ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሀዘን መታወጁን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን በጋጫ ባባ ወረዳ ላካ ቀበሌ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈውን ዜጐቻችንን በማስመልከት የሀዘን ቀን ታውጇል ብሏል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን በጋጫ ባባ ወረዳ ላካ ቀበሌ መጋቢት 2 /2018 ዓ.ም በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት ከ125 ሰዎች የ80 ወገኖቻችን ሕይወት አልፏል፤ ቀሪዎች በፍለጋ ላይ ይገኛሉ።
ምክር ቤቱ በዜጎች ላይ በተከሰተው አደጋ ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው ገልጿል። በኢትዮጰያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፕብሊክ የሰንደቅ አላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ (2) ብሔራዊ የሀዘን ቀን እና ስንደቅ አላማው የሚውለበለብባቸውን ሁኔታዎች የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፕብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ተደንግጐ ይገኛል፡፡
በዚሁ መሠረት በጋሞ ዞን ጋጫ ባባ ወረዳ ላካ ቀበሌ በመሬት መንሸራተት አደጋ ሕይወታቸው ያለፈው ዜጐቻችንን በማስመልከት ከመጋቢት 05/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለ3 ቀናት ብሔራዊ የሀዘን ቀን ታውጇል ብሏል።
በነዚህ ቀናት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ አላማ በሁሉም የሀገሪቱ ግዛቶች፣ በኢትዮጵያ መርከቦች በኢትዮጵያ ኢንባሲዎች እና ቆንጽላ ጽሕፈት ቤት ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ይህ ውሳኔ የተላለፈ መኾኑን እናሳውቃለን ብሏል በመግለጫው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
