
ባሕር ዳር: መጋቢት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት ከ33 እስከ 41 ዲግሪ ሴልሺየስ እንደሚደርስ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
ጋዜጣ ፕላስ እንደጻፈው በተያዘው ወር በመደበኛነት ከሚኖረው ከፍተኛ የፀሐይ ኃይል ጋር በተያያዘ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚመዘገበው የሙቀት መጠን ከፍተኛ ይኾናል።
በወሩ ትኩረት ከሚሹ የአየር ኹኔታ ክስተቶች መካከል በቀን የሚኖረው ከፍተኛ ሙቀትና በሌሊት የሚታየው ወበቅ ተጠቃሽ መኾናቸውን ትንበያው አመላክቷል።
በተለይም በምዕራብ አማራ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት ከ33 እስከ 41 ዲግሪ ሴልሺየስ እንደሚደርስ ትንበያው ያሳያል።
በሌላ በኩል በበልግ አብቃይ አካባቢዎች ከሚፈጠሩ ጠንካራ የደመና ክምችቶች በመጠንም ኾነ በሥርጭት የተሻለ ዝናብ እንደሚኖር ተመላክቷል።
በአንጻሩ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በኾኑት የደቡብና የደቡብ ምሥራቅ አካባቢዎች ከበልግ ወቅት የዝናብ ድርሻ እስከ 30 በመቶ የሚያገኙ ይኾናል። የመካከለኛውና የምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ደግሞ ከ20 እስከ 40 በመቶ የዝናብ ድርሻ እንደሚያገኙ ተጠቁሟል።
ከመጋቢት አጋማሽ በኋላ የወቅቱ ዝናብ አብዛኛውን የበልግ ተጠቃሚ እንደሚያዳርስ ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
