
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምርጫ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ በኾኑ አማራጮች መካከል አንዱን የመለየት ወይም የመወሰን ሂደት ነው።
በፖለቲካ ዘርፉ ምርጫ በአንድ ሀገር ውስጥ ሕዝቡ ሀገር የሚመራውን መሪ ወይም ተወካዮቹን ለመምረጥ የሚያደርገው ሂደት ነው።
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላም እና ደኅንነት መምህር እና ተመራማሪ ሙሉጌታ አየለ (ዶ.ር) አፍሪካን ጨምሮ በዓለም ላይ በምርጫ ሥርዓታቸው ጠንካራ የኾኑ ተሞክሮ ያላቸው ሀገራት መኖራቸውን ተናግረዋል።
ከአውሮፓ ኖርዌይ፣ ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ስዊድን፣ ጀርመን፣ ካናዳ እና ኒውዝላንድን በአብነት አንስተዋል። ከአፍሪካ ደግሞ ጋና፣ ቦትስዋና፣ ሞሪሽየስ እና ናሚቢያን በአብነት ጠቅሰዋል።
እነዚህ ሀገራት በምርጫ ሂደት ባለ ሥርዓት በማኅበረሰብ ተሳትፎ ነጻ እና ፍትሐዊ በመኾን፣ በሕግ የበላይነት፣ በምርጫ ግልጽነት፣ በምርጫ ታማኝነት፣ በዴሞክራሲ ልምምድ ተሞክሮ የሚወሰድባቸው እንደኾኑም ተናግረዋል። ምርጫን ሰላማዊ በኾነ ሁኔታ በማጠናቀቅ በድህረ ምርጫ ተግባራት፤ በሚዲያዎች የምርጫ አዘጋገብ ላይም አስተማሪ ታሪክ ያላቸው ናቸው ነው ያሉት።
አሚኮ ዲጅታል ሚዲያ ኢትዮጵያ ከእነዚህ ሀገራት ምን ትማር በሚል ለመምህር እና ተመራማሪው ላነሳላቸው ሀሳብ ኢትዮጵያ ካለፉት አምስት ምርጫዎች ልምድ በመውሰድ በስድስተኛው ምርጫ ከሌሎቹ ጊዜያት የተሻለ ሊባል የሚችል ምርጫ ማካሄዷን ጠቅሰዋል። በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመወዳደር የተመዘገቡ ፓርቲዎች ደግሞ የተሻለ የምርጫ ሥርዓት ሊኖራቸው እንደሚገባም መክረዋል።
የፓርቲ አባልነት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻውን ለምርጫ ውድድር መስፈርት ሊኾን እንደማይገባም አንስተዋል። ፓርቲዎች ምን ሀሳብ አላቸው የሚለው ጉዳይ ትኩረት የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የት ነው መሄድ የሚችለው? ሕዝቡ እንዴት ከድህነት ይወጣል? የነገዋ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን በምን መልኩ ታስጠብቃለች? የሚሉ ጉዳዮች ላይ በየዘርፋ ጠንካራ ክርክሮችን ማድረግ በሠለጠነ ዘመን ይጠበቃልም ብለዋል።
“የፓርቲዎች የምርጫ ክርክርም ግለሰብ ላይ ሳይኾን ሀሳብ ላይ ሊኾን እንደሚገባ” አስገንዝበዋል። በፖለቲካ ክርክር ላይ በልማድ ተይዘው የመጡ ጉዳዮች ሊኖሩ አይገባም ነው ያሉት። የተሻለ ሀሳብ አለኝ በሚል ሰበብ አንዱ ፓርቲ አንዱን ጥላቻ የሚቀባ እና የስሜት ፖለቲካ ሊኾን እንደማይገባም ተናግረዋል።
ነጻ እና ገለልተኛ የኾኑ፤ በራሳቸው የሚወስኑ ተቋማት መኖር እንዳለባቸውም መክረዋል። የሚዲያ እና የፖለቲካ ነጻነት መረጋገጥ እንደሚኖርበትም ጠቅሰዋል። ሚዲያዎች ነጻ እና ገለልተኛ ኾነው አሁን ላይ ያለውን መንግሥት ወካይ ፓርቲ እና ሌሎችን ተፎካካሪ ፓርቲዎች እኩል የመጠየቅ፣ የማፎካከር፣ የመከራከሪያ ሰዓት የመስጠት፣ በቀጥታ ሥርጭት በነጻነት ሀሳብ እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል።
ከምርጫ በኋላ የምርጫ ውጤትን የሚገልጹበት መንገድም ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል። ይህ ሲኾን የምርጫውን ሂደት ብቻ ሳይኾን የሚዲያን ታማኝነትም በይበልጥ ያጎላል ነው ያሉት።
ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ኾነ ገዥው ፓርቲ ከማንኛውም ነገር ነጻ ኾነው የምርጫ ሕጉን በማሰብ ውጤቱን መቀበል እና መተግበር እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
ከሁሉም በላይ ሕዝቡ በመንግሥትም ኾነ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ እምነት እንዲኖረው ምርጫው ሰለማዊ መኾን አለበት ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
