በኢትዮጵያ ያለው የመረጃ አጠቃቀም እና የማጣራት ክህሎት ምን ይመስላል?

9
ባሕር ዳር: መጋቢት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሚዲያ ንቃት (media literacy) ማለት በጽሑፍ፣ በምስል፣ በድምጽ እና በሌሎች የዲጂታል አማራጮች የሚተላለፉ መልዕክቶችን የመረዳት፣ የመተንተን እና የመገምገም ክህሎት ነው። ይህ ክህሎት መረጃን ከመቀበል በፊት “ለምን? በማን? እንዴት?…” ብሎ የመጠየቅ ልምድን ያዳብራል።
የሚዲያ ንቃት አንድ ግለሰብ የሚያገኘውን መረጃ ትክክለኛነት፣ እውነት ወይም ሐሰትን የሚለይበት እንዲኹም መረጃውን በንቃት የሚመረምርበት ክህሎት እንደኾነ በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህር አበራ የኔወርቅ (ዶ.ር) ይተነትናሉ።
መምህሩ ቀደም ባሉት ጊዜያት መረጃዎች በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ እና በጋዜጣ ብቻ የተገደቡ እንደነበሩ ገልጸዋል። በአሁኑ የዲጂታል ዘመን ግን ማንኛውም ግለሰብ መረጃ ማሠራጨት የሚችልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል። በዚህም መረጃን የማጣራት ክህሎት አስፈላጊነት እጅግ የጎላ መኾኑን ነው ያነሱት።
ፌስቡክ፣ ዩቲዩብ፣ ቲክቶክ በመሳሰሉ ማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩ መረጃዎችን እንዳለ የመቀበል እና የማሠራጨት ልምድ በመስፋፋቱ ሐሰተኛ መረጃዎች “እንደ ሰደድ እሳት” የመዛመት እድል ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት።
በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቁ መረጃዎችን የማጣሪያ በርካታ አማራጮች እንዳሉ ገልጸዋል።’ጉግል ሪቨርስ ኢሜጅ’ ወይንም ‘ጎግል ሌንስ’ የመሳሰሉ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም አንድ ፎቶ ከዚህ ቀደም የተለቀቀ መኾን አለመኾኑን ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስም (AI) የሰዎችን ድምጽ እና እንቅስቃሴ አስመስለው የሚሠሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማጣራት የሚያስችል ማጣሪያ ሶፍትዌሮች እንዳሉት ገልጸዋል።
የበለጸጉት ሀገራት የሚዲያ ንቃት ትምህርት በመስጠት ጠንካራ የመረጃ ማጣሪያ ተቋማት እንዳሏቸው ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የመረጃ ማጣራት ልምድን ግን ደካማ ብለውታል።
ውስንነቱም በተራው ማኅበረሰብ ዘንድ ብቻ ሳይኾን በሚዲያ እና በሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ጭምር የሚታይ መኾኑ አሳሳቢ ነው ባይ ናቸው።
የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል የወጡት አዋጅ ቁጥር 1185/2012 እና የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 ከሕግነት ባለፈ ተግባር ላይ እየዋሉ እንዳልኾነ አንስተዋል።
ኾን ብለው ሐሰተኛ እና አጥፊ መረጃዎችን ካሰራጩ እና የብዙኅኑን አዕምሮ ከበከሉ በኋላ ጉዳዩ ሲጋለጥ የለቀቁትን መረጃ ከማጥፋት ያለፈ ርምጃ ሲወሰድ እንደማይታይም ገልጸዋል።
መንግሥት አዋጆቹን በማስፈጸም ሐሰተኛ መረጃ አሰራጮችን በሕግ ተጠያቂ ሊያደርግ እንደሚገባ መምህሩ አሳስበዋል።
የተደራጀ የእውነታ አጣሪ ተቋማትን መፍጠር እና ለሚመለከታቸው አካላትም ሥልጠና መስጠት እንደሚገባም መክረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በጋሞ ዞን በተፈጥሮ አደጋ ሕይወታቸውን ባጡ ወገኖች የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ።
Next articleየምርጫ ክርክር ግለሰብ ላይ ሳይኾን ሃሳብ ላይ ሊኾን ይገባል።