ደም መለገስ ሕይወትን የማዳን ቅዱስ ተግባር ነው።

13
አዲስ አበባ፡ መጋቢት 04/2018 ዓ.ም(አሚኮ) የኢትዮጵያ ደም እና ኅብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት “መጋቢት የደም ልገሳ ወር” በሚል መሪ መልዕክት ሀገር አቀፍ የደም ልገሳ ንቅናቄን አስጀምሯል።
ተቋሙ በዚህ የንቅናቄ ወር ብቻ 40 ሺህ ዩኒት ደም ለመሠብሠብ ማቀዱን አስታውቋል። የኢትዮጵያ ደም እና ኅብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው እንደገለጹት በወሊድ፣ በድንገተኛ አደጋዎች እና በልዩ ልዩ ሕመሞች ምክንያት የደም ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል።
የመጋቢት ወር የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የጾም ወቅት በመኾኑ የለጋሾች ቁጥር እንዲቀንስ ማድረጉንም ጠቁመዋል።
ይህንን ክፍተት ለመሙላት እና ያጋጠመውን የደም እጥረት ለመቅረፍ መጋቢትን የደም ልገሳ ወር ማድረግ ማስፈለጉን አስረድተዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ከ322 ሺህ ዩኒት በላይ ደም በመሠብሠብ የበርካቶችን ነፍስ ማዳን መቻሉን ገልጸዋል። ዜጎች ይህን ክቡር ተልዕኮ በመረዳት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በንቅናቄ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ድኤታ ሳህረላ አብዱላሂ ደም ልገሳ በጾም ሂደት ላይ የሚፈጥረው ምንም ዓይነት የጤና ተፅዕኖ አለመኖሩን አስገንዝበዋል።
ጾምን መጾም የነፍስ ሥራ ሲኾን ደም መለገስ ደግሞ ሕይወትን የማዳን ቅዱስ ተግባር ነው ያሉት ሚኒስትር ድኤታዋ በአጽዋማት ወቅት የሚታየው የመለገስ መቀዛቀዝ ደም በሚፈልጉ ወገኖች ላይ ስጋት እየፈጠረ በመኾኑ ኅብረተሰቡ ሊረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የግል ተቋማትም ለዚህ ጥሪ ምላሽ እየሰጡ መኾናቸው ተገልጿል። የአቢሲንያ ባንክ የኢንተርፕራይዝ አገልግሎት ኦፊሰር መሠረት አስፋው ባንኩ ሠራተኞቹን እና ደንበኞቹን በማስተባበር ሀገር አቀፍ የደም ልገሳ መርሐ ግብር እንደሚያካሂድ አስረድተዋል።
ዘጋቢ፦ተመሥገን ዳረጎት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleያለ ሰላም ልማት፣ ትምህርት እና የኢኮኖሚ ዕድገት ሊመጣ አይችልም።
Next articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በጋሞ ዞን በተፈጥሮ አደጋ ሕይወታቸውን ባጡ ወገኖች የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ።