
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 04/2018 ዓ.ም(አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከደሃና ወረዳ እና ከአምደወርቅ ከተማ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ እየተወያዩ ነው።
የአምደወርቅ ከተማ ከንቲባ ያለው ወዳጅ የታጠቁ ኀይሎች በከተማው እና በወረዳው ጥፋት እንዳይፈጽሙ የወረዳው የጸጥታ ኀይል ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር ወረዳውን ከጥፋት መጠበቅ እንደቻለ ተናግረዋል።
የሚወድሙ የመሠረተ ልማቶች የሕዝብ በመኾናቸው፤ የሚዘጉ መንገዶች ኅብረተሰቡን ለችግር የሚያጋልጡ በመኾኑ ሰላምን ማጽናት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የሃይማኖት አባቶች መገዳደል ይብቃ እና ሰላምን እናስቀድም በማለት ታጣቂዎችን በመምከር የሰላምን አማራጭ እንዲቀበሉ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
ሁሉም የልማት ሥራዎች ከሰላም በኋላ ይደርሳሉ ያሉት አሥተዳዳሪው ሕዝቡ ሰላሙን ለማጽናት እየሠራ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ውይይቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እና ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መኾኑን አንስተዋል።
የአካባቢው የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የታጠቁ ኀይሎችን በማወያየት ጉዳትን ለመቀነስ እና የሰላምን አማራጭ እንዲቀበሉ ለማድረግ ላከናወኑት ተግባር አመሥግነዋል።
ያለ ሰላም እንቅስቃሴ፣ ልማት፣ ትምህርት፣ የኢኮኖሚ ዕድገት የማይመጣ በመኾኑ ሰላማችሁን ለማጽናት ልትሠሩ ይገባል ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት ለታጣቂዎች የሰላም አማራጭ በማቅረቡ በርካታ ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ መቀበላቸውን አንስተዋል። ይህንንም አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
በግጭቱ ምክንያት እሴት፣ ባሕል እና ታሪክ እየተሸረሸረ ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ መከባበርን በማስቀደም፣ ባሕልን በመጠበቅ እና በመደማመጥ የሀገርን ሕልውና ማስጠበቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
