
ባሕር ዳር: መጋቢት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰውን ጦርነት አስመልክቶ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ኢምባሲ በዚያው ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፏል።
ኢምባሲው በፌስ ቡክ ገጹ ባስተላለፈው መልዕክት ኢትዮጵያውያን ከተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የመንግሥት ተቋማት የሚወጡትን ሁሉንም መመሪያዎች እና ትዕዛዞች በመከተል ላይ መኾናቸውን ጠቅሶ አመስግኗል።
በቀጣይም በተለይ የድንገተኛ ጊዜ መልዕክት ወደ ስልክ በሚላክበት ጊዜ ባለመዘናጋት መመሪያዎችን ማክበራቸውን እንደሚያበረታታ ገልጿል።
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሕግ መሰረት ያልተረጋገጡ ወሬዎችን ወይም ይፋዊ ያልኾኑ መረጃዎችን ማጋራትና ማሰራጨት የሕግ ተጠያቂነት ያስከትላል። ኢትዮጵያውያን በየዋህነት ለሌላው ይጠቅማል በማለት እንኳን ቢኾን ያልተረጋገጡ መረጃዎችን እንዳያጋሩ አሳስቧል።
ከአየር ተመተው የወደቁ ስብርባሪዎችን ወይም አጠራጣሪ ነገሮች ከወደቁባቸው ቦታዎች ራቁ። የግድ አስፈላጊ ካልኾነ በስተቀር ተጋላጭ በኾኑ ስፍራዎች አትገኙ ብሏል።
ኢትዮጵያውያን ከወቅታዊ ኹኔታ ጋር በተያያዘ አስቸኳይ ድጋፍ ካስፈለጋቸውም በቀጥታ ስልክ ቁጥር +971500001522 በማንኛውንም ሰዓት (24/7) መደወል ወይንም በዋትሳፕ በጽሑፍ አሊያም በድምጽ መጠየቅ የሚችሉ መኾኑን አሳውቋል።
የአስቸኳይ ድጋፍ መስመሩ በመደበኛ ሥራ ጉዳዮች እንዳይያዝ ከወቅታዊ ኺኔታ ጋር ላልተያያዙ ጉዳዮች በተለመደው የኤምባሲ ቁጥር በመጠቀም እንዲተባበሩም ጠይቋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
