
አዲስ አበባ፡ መጋቢት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የካንሰር በሽታን ቀድሞ በመለየት እና ፈጣን መፍትሔ በመስጠት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን አስታውቋል።
በሳንባ እና በጽኑ ሕሙማን ሕክምና ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ “ሰው ሠራሽ አስተውሎትን እና የዲጂታል ጤና ፈጠራዎችን በመጠቀም የሳንባ እና የጽኑ ሕክምና አገልግሎትን ማዘመን” በሚል መሪ መልዕክት 12ኛ ዓመታዊ ኮንፈረንሱን አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ራሄል አራጋው እንደገለጹት ሰው ሠራሽ አስተውሎት በተለይም የሀብት ውስንነት ባለባቸው አካባቢዎች የካንሰር ሕመምን ቀድሞ በመለየት የሕክምና አሰጣጡን ቀልጣፋ እና ተደራሽ የማድረግ ትልቅ አቅም ይፈጥራል።
ልጃቸውን በካንሰር ካጡ በኋላ “ማቴዎስ ወንዱ ፋውንዴሽን”ን በማቋቋም ለ22 ዓመታት ሕዝባቸውን ያገለገሉት እና በአሁኑ ወቅት ራሳቸው የካንሰር ተጠቂ የኾኑት አቶ ወንዱ በቀለ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሕክምና ፋይዳው ትልቅ መኾኑን ገልጸዋል።
ካንሰር አስቀድሞ መከላከል እና መታከም የሚችል በሽታ በመኾኑ ሕሙማን ተስፋ ሊቆርጡ እንደማይገባም አሳስበዋል።
የጤና ሚኒስትር ድኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ መረጃን መሠረት ያደረገ ውሳኔ ለመስጠት እና ስኬታማ የጤና ሥርዓት ለመገንባት የዲጂታል ጤና ሥርዓት እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሚናቸው የላቀ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያደረገችው ያለው የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንት ሀገሪቱ የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለመኾን ለያዘችው ዕቅድ ትልቅ ድጋፍ እንደሚኾን ጠቁመዋል።
ጤና ሚኒስቴር ይሄን ዓላማ ለማሳካት የመረጃ አያያዝ ሥርዓቱን እና አስፈላጊ መሠረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በየዓመቱ እስከ 80 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በካንሰር በሽታ እንደሚያዙ ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በሽታውን ለመከላከል መንግሥት የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቶ እየሠራ ነው። በአሁኑ ወቅት 33 የካንሰር ኬሞቴራፒ ማዕከላት በሀገሪቱ ይገኛሉ።
ዘጋቢ ፦ሰላማዊት ነጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
