
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰሃላ ሰየምት ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ በቅንጅት እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል። የሰላም እጦቱ በክልሉ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት እያስከተለ በመኾኑ ሁሉም ለሰላም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።
ነዋሪዎቹ የሆስፒታል ግንባታ እና የመንገድ መሠረተ ልማት ችግር እንዲፈታም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ የወረዳው ሕዝብ የአካባቢውን ሰላም ለማጽናት እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
ሰላምን በማጽናት የዋግ ሕዝብ የአባቶቹን ታሪክ እያስቀጠለ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ሰላምን በማጽናት የበኩላችሁን ልትወጡ ይገባልም ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳይኖራት የሚተጉ ኀይሎች ውስጣዊ አንድነትን ለመበጥበጥ እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።
የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ አንድነትን ማጠናከር አስፈላጊ እንደኾነ ጠቁመዋል። ማኅበረሰቡ ሰላምን በማጽናት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ምርጫ የሀገር መንግሥት ግንባታ መሠረት ነው ያሉት ኀላፊው የምርጫ ካርድ በማውጣት የዜግነት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ሆስፒታል ላይ ያለውን የመሠረተ ልማት ችግርን ለማጥናት እና መፍትሔ ለማስቀመጥ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
የተከዜ የብረት ድልድይ ችግርንም ለመቅረፍ ትኩረት እንደሚደረግ አንስተዋል። የልማት ጥያቄዎቹን ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ ጋር በመኾን ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱ ይሠራል ነው ያሉት።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ማኅበረሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም አሳስበዋል።
ማኅበረሰቡ ከሥራ ኀላፊዎች ጋር በመቀናጀት የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል እና ሰላምን ማጽናት እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
