
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ባንክ ባወጣው መግለጫ በፋይናንስ ዘርፉ ያለውን ተወዳዳሪነት ለማስጠበቅ እየሠራ መኾኑን አስታውቋል።
ባንኩ በ2018 በጀት ዓመት በስምንት ወራት ውስጥ 1 ነጥብ 82 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡን ገልጿል። አጠቃላይ ሀብቱንም 52 ነጥብ 76 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል።
የአማራ ባንክ በፋይናንስ የተረጋጋ፣ ጤናማ አሠራር የዘረጋ፣ የብሔራዊ ባንክ ያወጣቸውን የቁጥጥር መመሪያዎችን በጥብቅ የሚከተል እና የሚያከብር መኾኑን አንስቷል። ባንኩ የቀን ከቀን ሥራውን የባንክ ቢዝነስ አሠራር መርኾዎችን እና መመሪያዎችን በመከተል እያከናወነ ነው።
በቅርቡ በአንዳንድ ሚዲያዎች የተሰራጩ ዘገባዎች የባንኩን የአሁናዊ ሁኔታ ያላሳዩ፣ የመደበኛ አገልግሎት የፋይናንስ አሠራር ሁኔታን በአግባቡ ያልተገነዘቡ፣ አብረውን የሚሰሩ ደንበኞቻችንን የማይመጥኑ እና የተሳሳቱ መረጃዎችን ለሕዝብ ያቀረቡ ኾነዉ ተገኝተዋል ነው ያለው በመግለጫው።
አማራ ባንክ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የባንኩን አሁናዊ እውነታዎች፣ ባንኩ ያሳየውን ቀጣይነት ያለዉ እድገት፣ የገነባዉን ጠንካራ የአሥተዳደር ሥርዓት እና በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ዙሪያ ግልፀኝነት ያለው አሠራር በማስፈን ረገድ ያለውን ቁርጠኛ አቋምና ተግባር ለማሳወቅ መግለጫውን ማውጣቱን አስታውቋል።
✍️ ጠንካራ የፋይናንስ አቅም እና የሃብት ጥራት
👉 አማራ ባንክ የብድር ፖርትፎሊዮና የክሬዲት ተጋላጭነቱን አስመልክቶ ሙሉ በሙሉ በብሔራዊ ባንክ በተላለፉ የጥንቃቄ መመሪያዎች ገደብ ውስጥ ኾኖ በመፈፀም ላይ ነው።
👉 የአማራ ባንክ ለአንድ ተበዳሪ የሚሰጠው ጠቅላላ የብድር መጠን ብሔራዊ ባንክ ከፈቀደው የቁጥጥር ገደብ የ25 በመቶ በታች ሲኾን፣ ይህም የብሔራዊ ባንክን የአደጋ ስጋት መመሪያዎችን በጥብቅ በመከተል የተፈጸመ ነው፡፡ ወደ ባንካችን መጥተው አሁን ላይ ብድር ከወሰዱ የግለሰብ ደንበኞች ከ20 በመቶ በላይ ባንኩ ብድር አላቀረበም።
👉 እ.ኤ.አ የ2025/26 በጀት ዓመት የስምንት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት መሰረት ባንኩ የሃብት ጥራቱን ለማጠናከር እና ለማሳደግ እየሠራ ነው፤ የተበላሸ ብድር ምጣኔ (NPL) መጠንን ወደ 4 ነጥብ 9 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህም በፋይናንስ ኢንዱስትሪው እና በብሔራዊ ባንክ ተቀባይነት ያለው መጠን ውስጥ እንዳለ የሚያሳይ ነው።
👉 ባንኩ የብድር ክትትል፣ የአመላለስ እና የማገገም ሥርዓቶች በመዘርጋቱ የፖርትፎሊዮ አፈፃፀሙ በከፍተኛ መጠን እንዲጠናከርና እንዲሻሻል አድርጓል። በዚህም ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ ከ9 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ከብድር መሰብሰብ ችሏል።
👉 ባንካችን ውስጥ የአደጋ ስጋት አሥተዳደር እና የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓቶች ቀጣይነት ባለው መልኩ እየተጠናከሩ ነው። ይህም ዘላቂነት ያለው የብድር አቅርቦት እንዲኖር በማገዝ ላይ ነው።
👉 ባንካችን በአሁኑ ሰዓት የተለየ የጥሬ ገንዘብ እጥረት የለበትም፤ ይህን ችግር ከፈታ ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በሞባይል ባንኪንግ አማካኝነት እስከ 1 ሚሊዮን ብር ድረስ ማስተላለፍ እንዲችሉ ማድረግ ተችሏል። ይህን በማድረግም አማራ ባንክ በተሻለ እርቀት መጓዝም ችሏል።
👉 ሌላው በዲጂታል አነስተኛ ብድር በርካቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ነው። በፋይናንስ አካታችነት ጉልህ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። በዚህም ባንኩ ከ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በዲጂታል አነስተኛ ብድር ሰጥቷል። ከዚህ ውስጥ 90 በመቶው ለሴት ተበዳሪዎች የቀረበ ነው። በአጠቃላይ በዲጂታል አነስተኛ ብድር ከ240 ሺህ በላይ ደንበኞች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
👉 ይህ ሁሉ ጥረት ባንኩ ጥንቃቄ ያለው የፋይናንስ አሥተዳደር እና ኀላፊነት ያለው የብድር ስርዓት እዳለው ያሳያል።
✍️ የስትራቴጂ ለውጥ ስለመደረጉ እና የባንኩ ዕድገት
ባንኩ በአሁኑ ወቅት የአምስት ዓመት የስትራቴጂያዊ ዕቅዱን በተግባር እያስፈጸመ ነው። ይህም የሥራ ብቃትን ለማሳደግ፣ የሚሰጣቸውን የፋይናንስ አገልግሎቶች ለማስፋፋት እና የረጅም ጊዜ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ሂደት ለማስቀጠል እየሠራ ነው።
የዚህ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ አካል ከኾኑትና ባንኩ ከወሰዳቸው አስፈላጊ አሥተዳደራዊ እርምጃዎች መካከል፦
👉 አዲስ መዋቅር በማስጠናት መተግበር ጀምሯል፡፡ እ.ኤ.አ ከመጋቢት1/2026 ጀምሮ አዲስ የደመወዝ ስኬል ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
👉 የተቀማጭ ገንዘብ እድገትን ለማፋጠን የሃብት ማሰባሰብ እንቅስቃሴዎችን በማስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡
👉 የባንኩን የአገልግሎት አሰጣጥና የውስጥ ክትትል ሥርአቶች ለማጠናከር እና ለማዘመን በመሥራት ላይ መኾኑም ይታወቃል።
✍️የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት
👉 አማራ ባንክ በተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ዘርፍ የሚያበረታታ ዕድገት እያሳየ ነው። የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ እስከ የካቲት 28 /2026 ድረስ ባሉት ቀናት 37 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ማድረስ ተችሏል። ይህም ባንኩ ላይ ሕዝቡ ያለው እምነት እየጠነከረ እና እያደገ መምጣቱን ያሳያል።
👉 ባንኩ የ2024/25 አፈጻጸምን መሰረት በማረግ ለባለአክሲዮኖቹ የትርፍ ክፍፍል (Dividend) ፈጽሟል። ይህም የባንኩ የፋይናንስ አፈፃፀም እየተሻሻለ መኾኑን እና ለባለአክሲዮኖቹ እሴት ለመፍጠር ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።
👉 እ.ኤ.አ ከሰኔ 2022 ሥራውን ከጀመረ ወዲህ ባንኩ አገልግሎቱን በማስፋፋት፣ የአሥተዳደር ስርዓቶችን በማጠናከርና ዘላቂ የፋይናንስ መሠረት በመገንባት ጉልህ እድገት አሳይቷል።
✍️ግልጽነት እና ኃላፊነት ያለው አገልግሎት ስለመስጠቱ
አማራ ባንክ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ግልጽነትን እና ኃላፊነትን ለማጠናከር ሚዲያ ያለውን ሚና ይገነዘባል። ሆኖም ግን በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚወጡ ዘገባዎች በተረጋገጡ እውነታዎች፣ በተቆጣጣሪ ተቋማት ግኝቶችና በሚዛናዊ አቀራረብ መመስረት እና መዘገብ አለባቸው።
በመኾኑም አማራ ባንክ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቋሙን የሥራ አፈጻጸም ለይፋዊ ኮምዩኒኬሽን በመጠቀም እና ለሕዝብ ከመድረሳቸው በፊት ኦዲት የተደረጉ የፋይናንስ ሪፖርቶችን መጠቀም፣ የብሔራዊ ባንክ የሚያወጣቸውን የቁጥጥር መግለጫዎችን እና መመሪያዎችን በመጠቀም መረጃዎችን ለሕዝብ እንዲያደርሱ ማድረግ ያስፈልጋል።
አማራ ባንክ አሁናዊ ቁመናው በፋይናንስ የተረጋጋ፣ ጤናማ አሠራር የዘረጋ እና በረጅም ጊዜ እድገት ላይ አተኩሮ እየሠራ ያለ ተቋም መኾኑን እናረጋግጣለን ብሏል በመግለጫው።
ባንኩ ራሱን ለማጠናከር እና ለኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ እድገት ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ ለማበርከት ከተቆጣጣሪዎች፣ ባለአክሲዮኖች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት መሥራቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
የዳይሬክተሮች ቦርድና ማኔጅመንቱ በጋራ የባለአክሲዮኖችን ሀብት መጠበቅ፣ የተቀማጭ ገንዘብ ደኅንነትን ማረጋገጥ፣ የሕግና የቁጥጥር መመያዎችን መከተል፣ የተቋማዊ አሥተዳደርን ማጠናከር እና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልማት የበኩሉን ድጋፍ የመስጠት ተግባራትን በመፈፀም ግልጸኝነትና ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ የባንኩን ቀጣይነት ያለዉ እድገት ለማስቀጠል የማይናወጥ ቁርጠኝነታቸውን ያረጋግጣሉ።
ደንበኞቻችን፣ ባለአክሲዮኖቻችን፣ ሰራተኞቻችን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ባለድርሻ አካላት ለአማራ ባንክ ስለሚያሳዩት ቀጣይነት ያለው እምነትና ድጋፍ ምስጋና ያቀርባል።
የአማራ ባንክ መግለጫ ማውጣት ያስፈለገው የባንኩን አሁናዊ ሁኔታ ባለአክሲዮኖቹ፣ ደንበኞቹ እና ኅብረተሰቡ በአግባቡ እንዲረዱት ለማድረግ መኾኑን ገልጿል።
በተመሳሳይ በባንኩ ላይ የተከፈተው የሚዲያ ዘመቻ ሆን ተብሎ በባንኩ ላይ ጫና ለማሳደር እና መደበኛ የባንክ አገልግሎቱን በአግባቡ እንዳይሰጥ ለማወክ እንደኾነ ለማሳወቅ ነውም ብሏል።
ባንኩ በጠንካራ እና የተረጋጋ የፋይናንስ አቋም ላይ ኾኖ እየሠራ እንደኾነ፣ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያዎችን መሠረት አድርገዉ እየተፈፀሙ እንደኾነ፣ ከሚዲያ ተቋማትም ጋር ቢኾን በግልጽነት እና መርህን ተከትሎ በአግባቡ እየሠራ እንደኾነ እና የባንኩን ባለአክሲዮኖችን፣ ደንበኞቹን እና ባለድርሻ አካላትን መብትና ጥቅም ባስከበረ አግባብ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደኾነ በድጋሚ ለማረጋገጥ ይወዳል ብሏል በመግለጫው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
