
አዲስ አበባ፡ መጋቢት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የስድስት አሥርት ዓመታትን ስኬታማ ጉዞ እያከበረ ነው።
የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ ተቋሙ ባለፉት ስድስት አሥርት ዓመታት በተፈጥሮ ጥበቃ መስክ ታላላቅ እና ታሪካዊ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
የሀገሪቱ የዱር እንስሳት ጥበቃ ጉዞ በ1958 ዓ.ም ተቋማዊ ቅርጽ በመያዝ መጀመሩን አስታውሰዋል።
በ1961 ዓ.ም የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክን በሕግ በማቋቋም የመጀመሪያውን ርምጃ ተራምዷል ነው ያሉት።
ዛሬ ላይ ግን በመላው ኢትዮጵያ በርካታ የጥብቅ ቦታዎች እንዲቋቋሙ ተደርጓል ነው ያሉት።
በተለይ የስሜን ተራራዎች እና የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርኮች ያላቸውን ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ መሠረት በማድረግ በዓለም ቅርስነት መመዝገባቸው ለሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዓለም አቀፍ ክብርን ያጎናጸፈ ስኬት መኾኑን ገልጸዋል።
ተቋሙ እነዚህን ቦታዎች በጥናት በማቋቋም ከክልሎች እና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር ሲጠብቅ እና ሲያለማ መቆየቱን ጠቁመዋል።
አሁን ላይም የሕግ ማስከበር፣ የሥነ ምህዳር ክትትል እና የቱሪዝም ሥራዎችን በልዩ ስትራቴጂ ከመመራት ባለፈ፣ በተመረጡ ቦታዎች ላይ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የዱር ሕይወትን እና የመኖሪያ አካባቢዎችን የመጠበቅ ጥረት ከኢትዮጵያ ቀደምት ታሪክ እና ባሕል ጋር የተቆራኘ መኾኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ይሁን እንጂ እያደገ ከመጣው የሕዝብ ቁጥር እና የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ፍላጎት አንጻር ዘርፉን ይበልጥ ማሳደግ እና ማላቅ የግድ እንደሚል አጽንኦት ሰጥተዋል።
በ60ኛው ዓመት ክብረ በዓል መርሐ ግብሩ ላይ የዘርፉን ስኬቶች እና ተግዳሮቶች የሚዳስስ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
