
አዲስ አበባ፡ መጋቢት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የተመሠረተበትን 60ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እያከበረ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትር ድኤታ ስለሺ ግርማ በዓሉ የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠበቅ ያለን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ መኾኑን ገልጸዋል።
“ዛሬ እኛ የምናከብረው ስድስት አሥርት ዓመታትን ያስቆጠረ የዱር ሕይወት ጥበቃ ሥራን ብቻ ሳይኾን በየዘመኑ በነበሩ አስተዋይ ዜጎች የተገነባ የብሔራዊ ቁርጠኝነት ታሪክን ነው” ብለዋል።
ተቋሙ ባለፉት 60 ዓመታት የኢትዮጵያን የዱር እንስሳት፣ የተፈጥሮ ሀብት እና ሥነ-ምህዳር ለመጠበቅ ቁልፍ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት አሥርት ዓመታት ጥብቅ ቦታዎችን በማቋቋም እና በማስፋፋት ረገድ ትልቅ ለውጥ ማሳየቷን የጠቀሱት ሚኒስትር ድኤታው ይህም ለዱር ሕይወት ጥበቃ ብቻ ሳይኾን ለሀገሪቱ ቱሪዝም እና ሳይንሳዊ ምርምር አዳዲስ ዕድሎችን መፍጠሩን አስረድተዋል።
በተለይም በዱር እንስሳት ቱሪዝም እና በኢኮ ቱሪዝም ዘርፍ የታየው ዕድገት ዓለም አቀፍ ጎብኝዎችን በመሳብ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ መጠንከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉ ተገልጿል።
ሕዝቡ ባሕላዊ የጥበቃ ሥርዓቶችን እና የአካባቢ ዕውቀትን በመጠቀም ዕውነተኛ የተፈጥሮ ሀብት ጠባቂ እና ለስኬቱ “አይተኬ” ሚና የተጫወተ የጀርባ አጥንት መኾኑን አንስተዋል።
ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ የዱር እንስሳት እና የተፈጥሮ ሀብት በተለያዩ ሰው ሠራሽ ችግሮች ስጋት ላይ መውደቃቸውን አስገንዝበዋል።
የመኖሪያ አካባቢ መራቆት፣ የሰው እና የዱር እንስሳት ግጭት፣ ሕገ ወጥ አደን እና የንግድ ዝውውር፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የፋይናንስ እና የቴክኒክ አቅም እጥረት ዋነኞቹ ተግዳሮቶች መኾናቸውን ጠቁመዋል።
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ጥበቃው ቀጣይነት ያለው የጋራ ጥረት፣ የፈጠራ ሥራ፣ ትብብር እና ሰፊ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ረጅም ጉዞ መኾኑንም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
