
አዲስ አበባ፡ መጋቢት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን “እንጠብቅሻለን አለብን አደራ” በሚል መሪ መልዕክት መገናኛ ብዙኃን ለብሔራዊ ጥቅም ያላቸውን ሚና በተመለከተ ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የሚዲያ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።
በኮንፈረንሱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የለውጡ መንግሥት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጽናት፣ የወል ትርክት እሴት ግንባታ እና የ150 ዓመታት የዘመናዊት ኢትዮጵያ ግንባታ ቁጭት የኾነውን ብልጽግና ማረጋገጥ በሚሉ አራት ዋና ዋና አምዶች ላይ በትኩረት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ብሔራዊ ጥቅም የአንድ ሀገር የሕልውና መሠረት መኾኑን የጠቆሙት አማካሪው ሚዲያ የዜጎችን ያገባኛል ባይነት እሳቤ በመገንባት በኩል ትልቅ ኀላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል።
ሀገር የሚገነባው በሕሊናዊ መንፈስ ነው፤ አባቶቻችን በዓድዋ ጦርነት ወቅት ለሉዓላዊነት መከበር ያሳዩት አንድነት ለዚህ ትልቅ ማሳያ መኾኑን ገልጸዋል።
በዚህ ዘመን ሀገር በሚዲያ ሲገነባ እና ሲፈርስ እየታየ መኾኑን ጠቅሰዋል። ቀደምት ጀግንነት እና ሀገር ወዳድነት በትውፊታዊ ሚዲያ እንደተገነባ ሁሉ የዛሬው ዘመናዊ ሚዲያም በሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ ጠንካራ ጡብ የማስቀመጥ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ ከመንግሥት የሪፎርም ርምጃዎች ወዲህ በሚዲያው ዘርፍ የፖሊሲ እና የሕግ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ገልጸዋል።
በዚህም የሚዲያ ተቋማት ቁጥር በ150 በመቶ መጨመሩን እና የሀሳብ ብዝኀነት እንዲፈጠር ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።
ሚዲያዎች በሀገር ሉዓላዊነት፣ በሕዳሴ ግድብ፣ በባሕር በር እና በዲፕሎማሲ ረገድ የሕዝብ ተሳትፎ እንዲረጋገጥ የሠሩትን ያህል አሁን ላይ የዲጂታል ሚዲያ መስፋፋትን ተከትሎ የሙያ ሥነ ምግባር መጣስ፣ የሐሰተኛ መረጃዎች መሰራጨት እና በሀገር ብሔራዊ ጥቅም ላይ ጉዳት የማድረስ ችግሮች እየታዩ መኾኑን ጠቁመዋል።
ኮንፈረንሱ በሚዲያው ዘርፍ በተፈጠረው ሰፊ ምህዳር ውስጥ ተቋማት በምን ያህል የኀላፊነት ስሜት እየተንቀሳቀሱ እንደኾነ የሚገመገምበት እና ለቀጣይ ሥራዎች የሚረዱ የጋራ ምክረ ሀሳቦች የሚቀርቡበት መኾኑም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሒም መሐመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
