
ባሕር ዳር: መጋቢት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዘመናችን የመረጃ ልውውጥ ከብርሃን ፍጥነት ጋር የሚፎካከርበት የዲጂታል ዘመን ላይ ይገኛል። ይህ የቴክኖሎጂ እድገት ይዞት ከመጣው በረከት ጎን ለጎን ለሀገር ብሎም ለዓለም የደኅንነት ሥጋት ኾኗል።
ሐሰተኛ መረጃ “የእውነትን” ዋጋ በማሳነስ የሰው ልጅ እርስ በእርስ እንዳይተማመን የሚያደርግ ማኅበራዊ መርዝ ነው።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት መምህር ጥላሁን ረጋ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ ሐሰተኛ መረጃዎች በስህተት ወይንም ኾን ተብሎ ተቀነባብረው የሚሰራጩ ሊኾኑ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
የተሳሳተ መረጃ (Misinformation) አብዛኛውን ጊዜ የሚፈጠረው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች አንድን መረጃ ሐሰተኛ መኾኑን ሳያውቁ “ለሌሎች ይጠቅማል ወይም ወቅታዊ ነው” በሚል ቅን እሳቤ ሲያጋሩ ነው።
ሌላኛው ሐሰተኛ መረጃ ደግሞ ኾን ተብሎ የሚሠራጭ የተዛባ መረጃ (Disinformation) ሲኾን የተለየ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሃብት ወይም ማኅበራዊ አጀንዳን ለማሳካት ታስቦበት የሚሠራጭ ነው። የሕዝብን ሥነ-ልቦና ለመስረቅ፣ ተቋማትን ለማፍረስ ወይም ግጭት ለመቀስቀስ ኾን ተብሎ የሚቀነባበር የጥፋት መንገድ እንደኾነም ነው መምህሩ የገለጹት።
መምህሩ እንዳብራሩት ሰው ሰራሽ አስተውሎትን (AI) ጨምሮ የተለያዩ የፎቶ እና የቪዲዮ ማቀነባበሪያ ሶፍትዌሮች መበራከት ሐሰተኛ መረጃ አምራቾች ሥራቸውን በቀላሉ እንዲከውኑ አድርጓቸዋል።
በአንድ የዓለማችን ጥግ የተፈጠረን ክስተት ወይም ምስል ኢትዮጵያ ውስጥ እንደተፈጠረ አስመስሎ በማሰራጨት ማኅበረሰቡን ለማሳሳት በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል። በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያው ዋነኛ ተጠቃሚ የኾነው የኅብረተሰብ ክፍል የመረጃውን ትክክለኛነት ለማጣራት የሚያስችል በቂ የሚዲያ እውቀት አይኖረውም። በዚህም የችግሩ ሰለባ እየኾነ ይገኛል ብለዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ግጭት በሚኖርባቸው ሀገራት ደግሞ ሐሰተኛ መረጃ በእሳት ላይ ቤንዚን የማርከፍከፍ ያህል አደገኛ መኾኑንም አንስተዋል።
በማኅበራዊ ሚዲያ የሚንሸራሸር ማንኛውንም መረጃ እውነትነት ለማረጋገጥ ፈቃድ ካላቸው እና ሙያዊ መርሕን ተከትለው ከሚሠሩ ሚዲያዎች ማረጋገጥ እንደሚገባም መክረዋል።
የተለያዩ የመረጃ አጣሪ ተቋማትን መከታተልና መረጃዎች ከየት እንደተለቀቁ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ማረጋገጥ ሌላኛው አማራጭ መኾኑን ተናግረዋል።
ተዓማኒ ሚዲያዎች ራሳቸው በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ጠንካራ ተሳትፎ ሊኖራቸው ይገባል። ዘመኑ የቴክኖሎጅ እንደመኾኑ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ ወጣቶች የሚዲያ አጠቃቀም ግንዛቤ እንዲኖራቸው መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በአጠቃላይ የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን የመግታት ኅላፊነት ያለው በእያንዳንዳችን ላይ ነው። ማንኛውንም መረጃ ከመገራቱ በፊት የመረጃውን እውነትነት፣ መረጃው ቢጋራ በሀገር ላይ የሚያስከትለው ጉዳት መመርመር የዜግነት ግዴታ ሊኾን ይገባል ሲሉም መምህር ጥላሁን አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
