
ዛሬ ከዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ኅብረት (ITU) ዳይሬክተር (ዶ.ር) ኮስማስ ዛቫዛቫ ጋር በዲጂታል ልማት ያለንን ትብብር ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት አድርገናል።
ሀገራችን ቴሌኮምን ጨምሮ በዲጂታል መሠረተ ልማት ተደራሽነት፣ በዲጂታል ክህሎትና በተቋም ግንባታ እንዲሁም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ የተገኙ ተጨባጭ ውጤቶች አስደናቂ መሆናቸውን የኅብረቱ ዳይሬክተር ገልጸውልኛል።
ይህንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ይበልጥ ለማፋጠን ከኀብረቱ ጋር ያለንን ትብብርም ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር የዛሬው ውይይት አበርክቶው ላቅ ያለ ነው።
ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን የመሪነት ሚና ማሳደግና የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ለዲጂታላይዜሽን፣ ዲጂታይዜሽንና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳችን ያለው ፋይዳ በተመለከተም ምክክር አድርገናል። የአቅም ግንባታ እና አዳዲስ የትብብር ዕድሎችን ማስፋት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም መክረናል።
በቀጣይም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ከግብ ለማድረስ እና ትብብራችንን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር በጀመርናቸው እና በሌሎች አዳዲስ ዘርፎች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ተስማምተናል።
በዘርፉ የሚደረጉ ዓለም ዓቀፍ ኮንፈረንሶችን በኢትዮጵያ በማዘጋጀት ሀገራችን ይበልጥ ስራዋን ለዓለም እንድትገልጥ በጋራ ለመሥራት እንዲሁም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እንዲሳካ ለመደገፍና በዘርፉ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚቀጥል ከስምምነት ላይ ደርሰናል።
