
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰውን ልጅ ከሚፈትኑት መሠረታዊ ጉዳዮች ውስጥ የጤና መታወክ ግንባር ቀደሙ ነው። የሳምባ ሕመም ደግሞ ጤናን ከሚያውኩት መካከል ተጠቃሽ ነው።
በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶክተር ማንአለ ጥላሁን የሳምባ ምች በባክቴሪያ እና በቫይረስ የሚከሰት ሳምባን የሚያጠቃ ሕመም ነው ብለዋል።
በይበልጥ ደግሞ እስከ አምስት ዓመት ዕድሜ ያሉ ሕጻናትን፣ ከ60 ዓመት በላይ ያሉ አዋቂዎችን እና ተጓዳኝ ሕመሞች ያሉባቸውን ሰዎች ያጠቃል ነው ያሉት። ሕመሙን ብዙ ጊዜ ማኅበረሰቡ በተለምዶ ብርድ መትቶኝ እያለ እንደሚጠራውም ገልጸውልናል። የበሽታው ሳይንሳዊ መጠሪያ የሳምባ ምች እንደኾነ ነው የጠቀሱት።
በመኖሪያ እና የሥራ አካባቢ ባልተረጋጋ የአየር ንብረት እና የሕክምና ማዕከሎች ላይ በሚኖር እንቅስቃሴ ምክንያት ሕመሙ ይከሰተል ብለዋል።
ብዙ ጊዜ ወቅቱ ከክረምት ወደ በጋ ሲቀየር ይፈጠራል ነው ያሉት። መስከረም ወር አካባቢ እና ከመጋቢት እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ ሕመሙ በብዛት ይኖራል ብለዋል።
በአካባቢ የሚመጣ የሳምባ ሕመም ደግሞ ብዙ ጊዜ የሚመጣው በነፋሻማ አየር ንብረት መኾኑንም ተናግረዋል። የተጠጋጋ አኗኗርም ለሳምባ ምች አጋላጭ እንደኾነ ጠቁመዋል።
ዕድሜያቸው ከፍ ያሉ ሰዎች ላይ ሁለት ሳምንት እና ከዛ በላይ ለኾነ ጊዜ የሚኖር ሳል፣ ደረት ላይ የውጋት ስሜት መኖር፣ የሰውነት ሙቀት መጨመር፣ የአተነፋፈስ መቀየር ምልክት እንደሚኖርም ተናግረዋል። ሕጻናት ላይ ደግሞ እነዚህ ምልክቶች እና የማልቀስ ሁኔታ ይኖራል ብለዋል።
የሳምባ ምች ሕመም ዓይነት እና ደረጃ እንደየ ሰዎች ዕድሜ እና በሕመሙ እንደተያዙበት መንስኤ እንደሚለያይም ገልጸዋል። ዝቅተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ የሚባሉ ደረጃዎች እንዳሉትም አንስተዋል።
ሕጻናት ላይ የአካል ምርመራ እና ከታካሚ የሕመም ታሪክ በመነሳት ምርመራ ይደረጋልም ብለዋል። ከአምስት ዓመት በላይ ለኾኑ ግን የደም፣ የአክታ፣ የሳምባ ራጅ (ኤክስራይ) ከፍ ሲልም የሲቲስካን ምርመራዎች ይደረጋሉ ነው ያሉት። የሚሰጠው ሕክምናም እንደ ሕመሙ ደረጀ እና የተከሰተበት አካባቢ እንደሚወሰን ተናግረዋል።
ዝቅተኛ ደረጃ ከኾነ በሽሮፕ መልክ፣ መካከለኛ ደረጃ ከኾነ ደግሞ በመርፌ ሕክምና ይሰጣል፤ ከፍተኛ ደረጃ ከኾነ ሕክምናውም ከፍ ይላል ነው ያሉት።
ከመድኃኒት ውጭም እንደየ ምልክቶቹ የሕክምና እገዛ ይደረጋል ብለዋል። ከአተነፋፈስ ጋር ተያይዞ በኦክስጅን የማገዝ፣ ከአመጋገብ ጋር ተያይዞ ግልኮስ የመስጠት እና የሰውነትን ሙቀት ለመቀነስ መድኃኒቶች እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
በባክቴሪያ የሚከሰት የሳምባ ምች ሕመም ባይታከም ገዳይ ነው ያሉት ዶክተር ማንአለ ተጠቂነታቸው ከፍተኛ ለኾኑት ደግሞ ገዳይነቱ ከፍ እንደሚል ተናግረዋል። ሕመሙ የግድ መታከም አለበት ነው ያሉት።
መኖሪያ ቤት እና የሥራ ቦታ ነፋስ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባም መክረዋል። የምግብ እጥረት ያለባቸው ሰዎችም ተጋላጭ ስለኾኑ አመጋገባቸውን ማስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ተጓዳኝ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸውም መክረዋል። ከ15 ቀን በላይ ተከታታይ ሳል ካለም ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
