ኢትዮጵያ በስድስት ወራት ውስጥ ቡናን ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ከ1ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አገኘች።

7

 

አዲስ አበባ፡ መጋቢት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ሚኒስቴር ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 200 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ ገበያ በመላክ 1 ነጥብ 35 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውቋል።

የግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮምዩኒኬሽን መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ይመር ዳውድ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በዓለም የቡና ንግድ ሥርዓት ውስጥ ከብራዚል፣ ቬትናም እና ከኮሎምቢያ ቀጥሎ 4ኛዋ ትልቅ የቡና አቅራቢ ሀገር ናት።

በአረቢካ ቡና መገኛነቷ ደግሞ የዓለምን 3ኛ ደረጃ ይዛለች። በዘርፉም ከፍተኛ የገበያ ተሳትፎ አላት።

የቡና ምርት በሀገሪቱ የውጭ ንግድ ገቢ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አስታውቀዋል። ባለፈው ዓመት 470 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 2 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን አስታውሰዋል። ይህም የ89 በመቶ የገቢ ዕድገት የታየበት ስኬታማ ዓመት ነበር ብለዋል።

ለተገኘው ውጤት በ2017 ዓ.ም የተመዘገበው የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን የገለጹት መሪ ሥራ አስፈጻሚው የአምራቾች የገበያ ተሳትፎም ከ40 በመቶ ወደ 80 በመቶ ከፍ ማለቱ ለውጤቱ መገኘት ሌላው ምክንያት መኾኑን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የቡና ምርት በስፋት እየቀረበ በመኾኑ የዋጋ መቀነስ እየታየ እንደኾነ ተናግረዋል።

በየካቲት ወር የነበረው የቡና ዋጋ ወደ 2 ነጥብ 81 ዶላር ዝቅ ብሏል። ወደፊትም እስከ 2 ነጥብ 77 ዶላር ሊወርድ እንደሚችል ግምት ተቀምጧል። በዚህም ምክንያት ምርት በስፋት ለዓለም ገበያ እየቀረበ በመኾኑ የቡና ዋጋ በእጥፍ ሊቀንስ እንደሚችል አንስተዋል።

አምራቾች እና የዘርፉ ተዋናዮች አሁን ያለውን የገበያ ዋጋ በመጠቀም ምርታቸውን በፍጥነት ለገበያ እንዲያቀርቡ አሳስበዋል።

ይህንን ሳያደርጉ ምርት የሚደብቁ እና የሚሰውሩ አካላት ላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከክልል የጸጥታ መሪዎች እና ከቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ እንደሚሠራ አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሕዝቡ ግጭትና ውድመትን በማውገዝ ሰላምን ተቀዳሚ አጀንዳው አድርጓል።
Next article‎”እያንዳንዱ ቀን የሀገሬን እና የሕዝቤን ታላቅነት ሳያረጋግጥ አይባክንም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር)