ማይክሮሶፍት የዊንዶውስ 10 ተጠቃሚዎች ኮምፒውተራቸውን ከጥቃት የሚከላከል ማሻሻያ አስተዋውቋል።

5

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ማይክሮሶፍት የዊንዶውስ 10 ተጠቃሚዎች ኮምፒውተራቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ የሚያስችል “KB5078885” የተሰኘ አዲስ የደህንነት ማሻሻያ ይፋ አድርጓል።

ምንም እንኳን ለዊንዶውስ 10 የሚደረገው መደበኛ ድጋፍ ቢቋረጥም፣ ማይክሮሶፍት ክፍያ ለሚከፍሉ ድርጅቶችና ተቋማት እስከ ጥቅምት 2028 ድረስ የሚቆይ “Extended Security Update (ESU)” የተሰኘ ልዩ የድጋፍ ፕሮግራም ማዘጋጀቱ ይታወቃል።

ይህ አሠራር ተቋማት ወደ ዊንዶውስ 11 ለመሸጋገር ተጨማሪ ጊዜ እንዲያገኙ ታሳቢ ያደረገ የሽግግር ጊዜ ነው። ይህ የቀረበው አዲስ ዝመና በዋናነት በኮምፒውተሮች ላይ የተገኙ 79 የደህንነት ክፍተቶችን ለመድፈን የወጣ ነው። ከእነዚህም ውስጥ ሁለቱ አስቀድሞ በጠላፊዎች እጅ ገብተው ጥቃት እያደረሱ የነበሩ አደገኛ ስጋቶች ናቸው።

በመኾኑም ይህንን ማሻሻያ መጫን የኮምፒውተሮች ደህንነት አስተማማኝ ለማድረግ ወሳኝ መኾኑን ማይክሮሶፍት አሳውቋል።

ከደህንነት ጥበቃው ጎን ለጎን፣ ዝመናው በአንዳንድ መሣሪያዎች ላይ ይታይ የነበረውን ያለመጥፋት (Shut down) ችግር ይፈታል።

ቀደም ሲል “System Guard Secure Launch” የሚባለው የደህንነት ሲስተም በሥራ ላይ በሚኾንበት ወቅት፣ ኮምፒውተሮች ሙሉ በሙሉ ለመጥፋት ወይም ወደ “Sleep” ኹኔታ ለመግባት ይቸገሩ ነበር፤ አዲሱ ማሻሻያ ግን ይህንን የቴክኒክ ስህተት ሙሉ በሙሉ አስተካክሎታል።

በተጨማሪም በቅርቡ ጊዜያቸው የሚያልፉ የደህንነት ሰርተፊኬቶችን በአዲስ በመተካት፣ ኮምፒውተራችን ለወደፊት ጥቃቶች እንዳይጋለጥ ያደርጋል።

ይህንን ማሻሻያ ለማግኘት በኮምፒውተሮች “Settings” ውስጥ በመግባት “Windows Update” የሚለውን መምረጥ፣ ከዚያም “Check for Updates” የሚለውን ትዕዛዝ በመጫን ማውረድና መጫን ይቻላል።

ማሻሻያው በተሳካ ኹኔታ ከተጫነ በኋላ የኮምፒውተራችሁ የጥበቃ ስሪት ወደ “Build 19045.7058” ከፍ ይላል። ማይክሮሶፍት እንደገለጸው ዝመናው ምንም ዓይነት የታወቀ የቴክኒክ ችግር ስለማያስከትል ተጠቃሚዎች በልበ ሙሉነት ሊጠቀሙበት ይችላሉ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበማኅበራዊ ሚዲያ የሚዘዋወረው የታሪፍ ማሻሻያው እውነት ነውን?
Next article“መሪዎች የሕዝብን ፍላጎት ማስቀደም ይኖርባቸዋል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)