የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለቀጣናው ሰላም እና ደኅንነት መረጋገጥ ስትራቴጂካዊ ነው።

3
አዲስ አበባ፡ መጋቢት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ)”ቀይባሕር እና የባሕርበር ለኢትዮጵያ ተፈጥሮአዊ መብት” በሚል መሪ መልዕክት ብሔራዊ የኢትዮጵያ ሠራዊት ማኅበር ያዘጋጀው ሀገራዊ ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በሲምፖዚየሙ ላይ አባት አርበኞች፣ የቀድሞ የሠራዊት አባላት፣ የመከላከያ ሠራዊት መሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። ብሔራዊ የኢትዮጵያ ሠራዊት ማኅበር ፕሬዝዳንት አምሳአለቃ ብርሃኑ አማረ ማኅበሩ በልማት፣ በሰላም፣ በጸጥታ እና በሌሎችም ሀገራዊ ጉዳዮች ከሕዝብ እና ከመንግሥት ጎን ኾኖ እየሠራ ይገኛል ብለዋል። ኢትዮጵያ እና ቀይ ባሕር ተለያይተው አያውቁም ያሉት ፕሬዝዳንቱ እኛም ለሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም በጋራ እንቆማለን ነው ያሉት። ማኅበሩ የቀይ ባሕርን የማስመለስ ጥያቄ ከጫፍ ለማድረስ የበኩሉን እንደሚወጣም ገልጸዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የትምህርት እና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኀላፊ ጄኔራል ይመር መኮነን ብሔራዊ የኢትዮጵያ ሠራዊት ማኅበር አባላት ሀገርን ከመበታተን ለመታደግ በተለያዩ ጊዜያት ሀገራቸውን ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ተናግረዋል። አሁንም በኢትዮጵያ የባሕር በር ይገባኛል ጥያቄ ላይ በንቃት በመሳተፍ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያ እና ቀይባሕር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ መኾናቸው የታሪክ ሀቅ፣ ተፈጥሮአዊ እና ሕጋዊ መብት መኾኑንም አንስተዋል። ኢትዮጵያ የባሕር በርን የመጠቀም የባለቤትነት መብቷን ስታረጋግጥ የቀጣናውን የንግድ ፍሰት ለማሳለጥ ወሳኝ እንደሚኾንም ገልጸዋል።
የባሕርበር ጥያቄ ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ ብቻ ሳይኾን የቀጣናውን ሰላም እና ደኅንነት ለማረጋገጥ ስትራቴጂካዊ ነውም ብለዋል። የኢትዮጵያ የባሕርበር ጥያቄ በዚህ ትውልድ እንዲመለስ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታውን ማየት ተገቢ መኾኑም ተነስቷል። የኢትዮጵያ የባሕርበር ባለቤትነት መብት ላይ ያተኮረ ለውይይት መነሻ ጹሑፍ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል። የኢትዮጵያን የባሕርበር ባለቤትነት በተመለከተ በመላው ሀገሪቱ ባሉ 305 ቅርንጫፎቹ ተመሳሳይ ንቅናቄ ይካሄዳልም ተብሏል።
ዘጋቢ፦ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የባሕሩን ታሪክ የት ይደብቁታል፣ እንኳንስ ሰዎቹ ግመሎች ያውቁታል”