
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ እዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል መሐመድ ተሰማ እና የእዙ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ሜጄር ጀነራል ተስፋዬ ረጋሳ በጎጃም ተሰማርቶ ውጤታማ ግዳጅ እየተወጣ ከሚገኝ የጦር ክፍል መሪዎች እና አባላት ጋር ተገናኝተው ግዳጅ ሰጥተዋል፡፡
የምሥራቅ እዝ አዛዥ ሌተናል ጀነራል መሐመድ ተሰማ የኢትዮጵያ ሠራዊት በማንኛውም የጸጥታ ችግር ባለበት የኢትዮጵያ ክልል ተሰማርቶ ሕዝብን አደጋ ላይ የሚጥል የጸጥታ ችግሮች እና ችግር ፈጣሪዎች ላይ ርምጃ በመውሰድ ሕግ ማስከበር ዋነኛ ተልዕኮው ነው ብለዋል። እናንተም የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ ያደረጋችሁት ተጋድሎ ክብር የሚሰጠው ነው ብለዋቸዋል፡፡ እኛ የምንዋጋው ከኢትዮጵያ ጠላቶች ነው፤ እኛ ለሕዝብ ችና ለሀገር የምንከፍለው መስዋዕትነት ክብር ነው፤ የኛ ድካም እና መንከራተት ለሕዝብ እና ለሀገር ነው ብለዋል። እነሱ ግን ለመዝረፍ እና ሀገርን አሳልፎ ለመስጠት ነው ያሉት አዛዡ የምንዋጋበት ዓላማ ፍትሐዊ ስለሆነ ሁልጊዜም አሸናፊዎች ነን፤ ድልንም እየተቀዳጀን መጥተናል ነው ያሉት።
ጽንፈኛው በአሁኑ ሰዓት ቀበሌ ይዞ መቆየት የማይችልበት ደረጃ የደረሰው በሠራዊቱ ብርቱ ትግል እና ድል መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ ውጤት በመመዝገቡ የጎጃም ሕዝብ ለሠራዊቱ ያለውን ፍቅር እየገለጸ መኾኑን አንስተዋል።
ሕዝባችን በዓላት ሲመጡ ያለችውን ከኛ ጋር ተካፍሎ ይበላል ያሉት አዛዡ ሕዝቡ ለኛ መረጃ በመስጠት እነሱን መረጃ በመከልከል ሂዱ አንፈልጋችሁም ማለት ጀምሯል ነው ያሉት። ሕዝቡ ለሚሠራው ሕግን የማስከበር እና የሀገር ሉዓላዊነትን የማስጠበቅ ግዳጅ ሁነኛ የጀርባ አጥንት መኾኑን ገልጸዋል።
በዚህ ምክንያት ጽንፈኛው በደንብ እንዲመታ ፣ አደረጃጀቱ እንዲፈርስ እና እንዲሟሽሽ ኾኗል ነው ያሉት። በትንንሽ ቡድኖች ኾኖ ሠራዊቱ በማይደርስበት አካባቢ ራሱን እየደበቀ የዝርፊያ ሥራን የሙጥኝ ማለቱንም ገልጸዋል። ጽንፈኛው ከኢትዮጵያ ሁነኛ ጠላቶች የሚወረወርለት ፍርፋሪ እንዳይደርቅበት፣ የእነርሱን አጀንዳ ለማስፈጸም ላይ ታች ቢልም፣ የኢትዮጵያ ጠላቶችን ፍላጎት በተዘዋዋሪ ለማሳካት ቢታገልም ሕዝቡ ከጎናችን በመኾኑ ሕልሙን በማጨለም እና በማምከን አንፃራዊ ሰላም ማረጋገጥ ችለናል ነው ያሉት።
የተሰጣችሁን ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮ በማንኛውም ቀጣና እና በየትኛውም የአየር ፀባይ ተሰማርታችሁ ጽንፈኛውን የገባበት ገብታችሁ በመደምሰሳችሁ ልትኮሩ ይገባል ብለዋል። ይህ ጠላትን አድኖ ፣ አሳዶ እና ከቦ የመደምሰስ ግዳጅ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። መንግሥት አሠልጥኖ ፣ አስታጥቆ ፣ ግዳጅ ሰጥቶ አሰማርቶናል ያሉት አዛዡ እኛም ጽንፈኛውን ቡድን ፈልገን፣ አስሰን እና አዛብተን መደምሰስ ይጠበቅብናል ነው ያሉት። ግዳጃችንን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ኢትዮጵያ የምትፈልገን ቦታ ለመገኘት ዝግጁነታችንን ማጠናከር ይጠበቅብናል ብለዋል።
ውትድርና ብዙ ሰዎች እንደ አንድ ፣ አንድ ሰው እንደ ብዙ ግዳጅ የሚወጣበት የሙያ መስክ መኾኑንም ገልጸዋል።
ከምሥራቅ እዝ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው አቅሞችን አቀናጅቶ በመጠቀም ውጤታማ እና ሊነገር የሚችል ታሪክ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
