ሀገራዊ የምርት እድገትን በሚያሻሽሉ ተግባራት ላይ በትኩረት እየሠራ መኾኑን ፀደይ ባንክ አስታወቀ።

7
ባሕር ዳር: መጋቢት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ፀደይ ባንክ የሀገርን አጠቃላይ የምርት እድገት በሚያግዙ ዘርፎች ላይ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል አስታውቋል፡፡
የባንኩ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ.ር) ባንኩን ወደተሻለ ውጤታማነት በሚያሸጋግሩ ጉዳዮች ላይ ከዲስትሪክት፣ ከቅርንጫፍ ሥራ አሥኪያጆች እና ከቡድን መሪዎች ጋር ተወያይተዋል። ፀደይ ባንክ የብድር ሥርጭቱን በማስፋት ማይክሮ፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ወደተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በሚያስችሉ ዘርፎች ላይ መሥራቱ ገልጸዋል። በእነዚህ ተግባራት ላይ በቀጣይ በትልቁ መሥራት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ለሀገር አጠቃላይ የምርት እድገት እና ለማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ከፍተኛ ድርሻ ላላቸው ዝቅተኛ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሰጠውን ትኩረት ይበልጥ ማስፋት እንደሚገባም አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

የባንኩን ጥሬ ገንዘብ በአግባቡ ማሥተዳደር፣ ብድር ማስመለስ፣ የተለያዩ አማራጮችን በማስፋት የባንኩን የሃብት አሠባሠብ ማሳደግ እና የውጭ ምንዛሬ ክምችትን ማሳደግ የሚሉት ዐበይት ጉዳዮችም ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ተብሏል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ከባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ታቦር፣ እንጂባራ፣ ፍኖተ ሰላም እና ደብረ ማርቆስ የዲስትሪክት፣ የቅርንጫፍ ሥራ አሥኪያጆች እና የቡድን መሪዎች ጋር በባሕር ዳር ከተማ ተወያይተዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ከደሴ፣ ወልድያ፣ ሰቆጣ እና ደብረ ብርሃን የዲስትሪክት፣ የቅርንጫፍ ሥራ አሥኪያጆች እና የቡድን መሪዎች ጋር በኮምቦልቻ ከተማ ውይይት ተካሂዷል። በቀጣይ ደግሞ አዲስ አበባ ዲስትሪክ ጋር የማጠቃላያ ውይይት ይካሄዳል ነው የተባለው። የውይይቱ ተሳታፊዎችም ወቅቱን የጠበቀ ሰፊ ምክክር መካሔዱን ገልጸዋል። መድረኩ መነቃቃትን የፈጠረ እና ለተሻለ ውጤት የሚያነሳሳ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ከ12 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉት ፀደይ ባንክ ካሠራጨው 49 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ብድር ውስጥ ከ39 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ለማይክሮ፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በማሠራጨት ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት እድገት ዐሻራውን እያሳረፈ የሚገኝ ባንክ ነው፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleለውጥ ያመጡ የግብርና ምርምር ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
Next articleየሽቦ መኪና መሥራት ወይስ የካርቶን ጠመንጃ መሸከም?