የባሕር በር የትውልድ ሕልውና ነው።

13
ባሕርዳር፡ የካቲት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎የአፍሪካ ቀንድ ስትራቴጂካዊ የኾነው የቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ መገኛ በመኾኑ ለዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ወሳኝ መተላለፊያ በር ነው። በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአፍሪካ እና በአውሮፓ መካከል እንደ ድልድይ ኾኖ የሚያገለግል ወሳኝ ቀጣናም ነው።
የዓለም ኀያላን ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ በቀጣናው ልዩ ፍላጎት አላቸው። በዚህ ስትራቴጂካዊ ስፍራ ኢትዮጵያም የቀጣናው ጂኦ-ፖለቲካ ማዕከል ናት። ካላት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር፣ ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ተሰሚነት እና ወታደራዊ አቅሟ አንጻር የቀጣናው መልሕቅ ኾናም ታገለግላለች።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ብሔራዊ ጥቅም አስጠብቃ ለመቀጠል የባሕር በር ባለቤትነት ወሳኝ ጉዳይ እንደኾነ ይነሳል። የባሕር በር ለኢኮኖሚ ዕድገት ብቻ ሳይኾን ለብሔራዊ ደኅንነት እና ለሀገር ሉዓላዊነት ቁልፍ ጉዳይ ተደርጎ ይወሰዳል። የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የሕልውና እና የብሔራዊ ጥቅም መሠረት መኾኑንም ምሁራን ይናገራሉ።
በጅንካ ዩኒቨርሲቲ የፓለቲካል ሳይንስ መምህር ምስክር ከተማ ኢትዮጵያ በታሪኳ የባሕር በር ባለቤት የነበረች ቢኾንም ፍትሐዊ ባልኾነ መንገድ ማጣቷን አንስተዋል። የአሁኑ ጥያቄዋም ዓለም ዓቀፋዊ ሕግን የተከተለ፣ ታሪካዊ ዳራ ያለው፣ ፍትሐዊ እና ተገቢ መኾኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ተፅዕኖ ለማስቀጠል እና በቀይ ባሕር ነባር ይዞታዋን ለመመለስ የውስጥ አንድነትን ማጠናከር፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር መልካም ትብብር መመስረት እንደሚያስፈልጋት አንስተዋል።
የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች ከጎረቤቶች በመነጠል ከኢትዮጵያ ጋር እንዲሰለፉ የሚያደርግ ስልትን መከተል ያስፈልጋል ብለዋል።
እንደ መምህሩ ማብራሪያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ሰላማዊ ግንኙነትን በሚያጠናክር መንገድ ትብብርን መመሥረት ያስፈልጋል። ስጋትን ሳይኾን ዕድልን ይዞ እንደሚመጣ ለጎረቤቶቿ ማስገንዘብ፣ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርጉ አካሄዶችን መከተል እንደሚገባም አንስተዋል።
በኢኮኖሚ የሚያስተሳስሩ የጋራ መሠረተ ልማቶችን ማሥፋፋት፣ ተመጋጋቢ ኢኮኖሚን መፍጠር ጎረቤት ሀገራት ተባባሪ እንዲኾኑ ለማድረግም ያስችላል ነው ያሉት። ጠንካራ የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚን መገንባት፣ ሉዓላዊነትን መጠበቅ እና የውስጥ አንድነትን ማረጋገጥ ወሳኝ መኾኑንም አብራርተዋል።
የባሕር በር ጉዳይ ከአንድ መንግሥት ወይም የፖለቲካ ሥርዓት ያለፈ የትውልድ ጥያቄ በመኾኑ ከፍ አድርጎ መገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ይህንን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ጠንካራ የዲፕሎማሲ መንገድ በመከተል ለዓለም ዓቀፉን ማኅበረሰብ በሚገባ ማስገንዘብ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል። ለዚህም ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መላው ዜጋም ርብርብ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የባሕር በር ጉዳይ የቀጣዩ ትውልድ ሕልውና ጉዳይ እንጂ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም ያሉት መምህሩ የመንግሥት ፍላጎት ብቻ ሳይኾን የሕዝብ ደኅንነት እና የሀገር ሕልውና ጉዳይ ነው ይላሉ። በዚህም ሁሉም ዜጋ ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) በሀረሪ ክልል ሶፊ ወረዳ የተሠራውን የገጠር ኮሪደር ጎበኙ።
Next articleለውጥ ያመጡ የግብርና ምርምር ሥራዎች እየተሠሩ ነው።