
ባሕር ዳር: የካቲት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምርጫ ሂደት ሀሰተኛ መረጃ የዜጎችን የመምረጥ መብት በመጋፋት እና በዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ላይ ጥርጣሬን በመፍጠር የምርጫን ተዓማኝነት በእጅጉ ይጎዳል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ከማኅበራዊ ሚዲያ አንጻር የሚስተዋሉ ችግሮችን ማጤን እና መቋቋም ከሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ይጠበቃል።
በተለይ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች የኅብረተሰቡን አመለካከት በመቅረጽ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ይታመናል። የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው ወጣት ብርሃኑ አማረ በሁሉም የሚዲያ መድረኮች መረጃዎችን በማጋራት እና በመከታተል በንቃት እንደሚሳተፍ ተናግሯል።
ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ወጣቶች ስለ ምርጫ ግንዛቤ እንዲኖራቸው፤ ምዝገባ እንዲያደርጉ የማነሳሳት፤ ምርጫ ማድረግ ለሀገር ስላለው ጠቀሜታ፤ የሀሰተኛ መረጃ ሥርጭትን መዋጋት እንደሚያስፈልግ እና ትክክለኛ መረጃ በማሠራጨት በኩል አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑንም ገልጿል።
ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ምርጫን የሚመለከቱ መረጃዎች በስፋት እንደሚሠራጩ ያነሳው ወጣቱ ነገር ግን የሚለቀቁ መረጃዎች ሁሉ እውነት ላይኾኑ እንደሚችሉ መገንዘብ ያስፈልጋል ብሏል።
ማኅበረሰቡ እውቅና የተሰጣቸውን እና ተጠያቂነትም ያለባቸውን የመገናኛ ዘዴ ገጾችን በመከተል ራሱን ከሀሰተኛ መረጃዎች ማራቅ እንደሚገባውም አሳስቧል።
ሌላኛዋ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ወጣት ቤተልሔም በሁሉም ምርጫ እየተቃረበ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ የተለያዩ መረጃዎች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲለቀቁ ማስተዋሏን ተናግራለች። ነገር ግን ስለ ምርጫውም ኾነ ስሌሎች ጉዳዮች አወንታዊ ሀሳቦችን ብቻ መርጣ እንደምታነብ ነው የገለጸችው።
ኢትዮጵያ ብቁ አምራች እና ሀገር ተረካቢ ወጣት ያስፈልጋታል ያለችው ወጣቷ ትኩሱ ኃይል የተሳሳተ መረጃ ይዞ ወደ ጥፋት ማምራት እንደሌለበት ተናግራለች። ይልቁንም ለሀገር እና ለሕዝብ የሚጠቅም ጉዳይ ላይ ማተኮር እንደሚጠበቅበት አስገንዝባለች።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
