
ባሕር ዳር: የካቲት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ብሔራዊ ጥቅም አንዲት ሉዓላዊት ሀገር ሕልውናዋን ለማስቀጠል፣ ደኅንነቷን ለመጠበቅ፣ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት እና የማኅበራዊ ደኅንነትን ለማረጋገጥ የምትቀርጸው መሠረታዊ ግብ ነው።
ጽንሰ ሃሳቡ በአንድ ሀገር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና በውስጥ ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች ላይ እንደ መሪ ኮምፓስ የሚያገለግል ነው ማለት ይቻላል።
የሀገርን ሕልውና የመጠበቅ እና የዜጎቿን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ዓላማ ያለው መኾኑንም የፖለቲካ ምሁራን ይገልጻሉ።
በብሔራዊ ጥቅም እሳቤ መሠረት የግዛት አንድነትን መጠበቅ፣ ሉዓላዊነትን ማስከበር እና የሕዝብን ደኅንነት ከውጭ ወረራ መከላከል ለድርድር የማይቀርቡ እና በጊዜ ሂደት የማይለወጡ ቋሚ ጉዳዮች ናቸው።
ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና እንደ ንግድ አጋርነት ያሉ ጥቅሞች ደግሞ እንደ ዓለም አቀፉ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሁኔታ ሊለዋወጡ ይችላሉ።
በመኾኑም አንዲት ሀገር ብሔራዊ ጥቅሟን በብቃት ለማስከበር በውስጥ የሚኖራትን አንድነት ማጠናከር እና በውጭ ደግሞ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በሰጥቶ መቀበል መርሕ ላይ በመመሥረት የራሷን የበላይነት በሰላማዊ መንገድ የምታረጋግጥበትን ጥበብ መከተል ይኖርባታል።
በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ካሳሁን አበራ የአንድ ሀገር ሕልውና፣ ክብር እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት በዋናነት የሚለካው ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር በምትከተለው ፖሊሲ እና የዲፕሎማሲ ስልት ነው ይላሉ።
ብሔራዊ ጥቅም ማለት አንድ ሀገር በየትኛውም ዓለም አቀፍ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብት እና የማኅበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ ቅድሚያ ለሀገር የምትሰጥበት እና ሉዓላዊነቷን የምታስከብርበት ጽንሰ ሐሳብ ነው ብለዋል።
ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ሀገራት የተለያዩ የዲፕሎማሲ መንገዶችን ይጠቀማሉ። በአንድ በኩል በወታደራዊ አቅም ላይ የተመሠረተ “ኃይል አዘል ዲፕሎማሲ” ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ በማሳመን፣ በድርድር እና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ ለስላሳ ዲፕሎማሲ መርህ መኖሩን ነው የተናገሩት።
ጠንካራ ምጣኔ ሃብት እና ወታደራዊ አቅም ያላቸው ሀገራት ብዙውን ጊዜ ኃይል አዘል ዲፕሎማሲን ሲመርጡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት ደግሞ በማሳመን እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተውን ለስላሳ ዲፕሎማሲ መከተል አዋጭነቱ የጎላ ነው ይላሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በብቃት ለማስጠበቅ የውስጥ አንድነትን እና ምጣኔ ሀብትን ማጠናከር ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠበቃል።
የውስጥ ሰላምን ማስፈን በዋና ዋና ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ከተቻለ እና የምጣኔ ሀብትን ማጠናከር ከተቻለ የውጭ ጥገኝነትን በመቀነስ በራስ መተማመንን መገንባት እንደሚቻል ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያን የነጻነት ታሪክ፣ የፓን አፍሪካኒዝም መሪነት እና ባሕላዊ ቅርሶችን እንደ ዲፕሎማሲያዊ መሣሪያ መጠቀም ይገባል።
ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ወይንም በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን የሀገር ገጽታ ግንባታ እና የምጣኔ ሃብታዊ አቅም አካል ማድረግ እና የጋራ ተጠቃሚነት መርሕ መከተል ይገባልም ብለዋል።
ጎረቤት ሀገራትን በምጣኔ ሀብት እና በመሠረተ ልማት በማስተሳሰር የእነሱን ብሔራዊ ጥቅም ከኢትዮጵያ ሰላም ጋር እንዲቆራኝ ማድረግ ሌላኛው መንገድ ነው።
የሀገራትን ስትራቴጂካዊ ጥምረት ሚዛንን መጠበቅ እንደሚገባም አንስተዋል። በዘመናዊው ዓለም ብሔራዊ ጥቅም የሚጠበቀው በመረጃ ብልጫ ጭምር እንደመኾኑ የመረጃ እና የቴክኖሎጂ አቅምን መገንባት ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
