
ባሕር ዳር: የካቲት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ እዝ ውጤታማ የሥራ አፈጻጸም ላስመዘገቡ እና የመቆያ ጊዜያቸውን ለሸፈኑ ከባለ ሌላ ማዕረግተኛ እስከ ከፍተኛ መኮነን ለኾኑ የእዝ ስታፍ የሠራዊት አባላት ማዕረግ አልብሷል።
በልዩ ዘመቻ ማሠልጠኛ ማዕከል ሥልጠናቸውን አጠናቅቀው ለመጡ የኮማንዶ አባላትም አቀባበል ተደርጓል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የምሥራቅ እዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሃመድ ተሰማ በዓድዋ የድል በዓል ማግሥት ጀግኖቻችን የማዕረግ ዕድገት ማግኘታችሁ ዕድለኛ ያደርጋችኋል ብለዋል።
ውትድርና የአንድ ሀገር ዜጎች እና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ መተኪያ የሌላትን ሕይወት በመክፈል ሀገራዊ ተልዕኮን ለመወጣት ቆርጠው ለመስዋዕትነት የተዘጋጁ ምርጥ ዜጎች የሚሳተፉበት ምርጥ ሙያ መኾኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከሀገረ መንግሥት ምስረታ ጀምሮ እስካሁን በዚህ የተከበረ ሙያ በርካታ መስዋዕትነት እየከፈሉ ሀገርን ያስቀጠሉ ጀግኖች እንዳሏት ተናግረዋል።
ጀግኖች አሁን ላለነው ትውልድ ያስረከቡን ክብር የምንሰጠው ሙያ ስለኾነ እኛም ድርሻችንን እየተወጣን እንገኛለን ነው ያሉት።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ጀግኖች ልጆቿ በሚከፍሉት መስዋዕትነት ጠላቶቿን እያሳፈረች፣ በመንግሥት እና
በታታሪው ሕዝብ ትግል የድህነትን ተራራ እየናደች መኾኗን አንስተዋል። ዓለምን የሚያስደምሙ ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በመገንባት በዕድገት ጎዳና ላይ መኾኗንም ገልጸዋል።
እኛ የኢትዮጵያ ወታደሮች የገባነውን ቃል ኪዳን፣ የአያቶቻችን እና የአባቶቻችን አደራ ተረክበን ከኛ የሚጠበቀውን መስዋዕትነት በመክፈል ጠላቶቻችንን እያሳፈርን በድል እየተወጣን ያለን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚኮራብን የኢትዮጵያ ወታደሮች ነን ብለዋል።
ማዕረግ የለበሱ መሪዎች የቆይታ ጊዜያቸውን በሚገባ የሸፈኑ፣ በሥራ አፈጻጸማቸው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የዛሬ ተሿሚዎች የተሰጣችሁ ማዕረግ ተጨማሪ ኀላፊነት መኾኑን አውቃችሁ ዕውቀት እና ክህሎታችሁን በመጨመር ያለፍናቸውን የውጊያ ተሞክሮ እንደ ግብዓት በመጠቀም ለቀጣይ ተልዕኮ መዘጋጀት ይጠበቅባችኋል ብለዋል።
የኮማንዶ አባላትም ውስብስብ እና እልህ አሰጨራሽ ሥልጠናችሁን አጠናቃችሁ ወደ እናት አሃዳችሁ ስለመጣችሁ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።
በወሰዳችሁት ሥልጠና መሠረት በሚሰጣችሁ የውጊያ አውድ ላይ ለየት ያለ ኦፕሬሽን በሚጠይቁ ግዳጆች ላይ በአጭር ጊዜ ድል እንደምታስመዘግቡ እርግጠኛ ነኝ ነው ያሉት።
ምሥራቅ እዝ እናንተ ሳትመጡ በርካታ ስምሪቶች አድርጎ ውጤቶችን አስመዝግቧል ያሉት አዛዡ የእናንተ አቅም ሲጨመር እዙ ተጨማሪ ውጤቶችን እንደሚያስመዘግብ አምናለሁ ብለዋል።
ተሿሚዎችም በተሰጣቸው የማዕረግ ዕድገት ደስተኞች መኾናቸውን ተናግረዋል። ከምሥራቅ እዝ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በተሰጣቸው ኀላፊነት እንደ መሪ የታችኛውን የጦር ክፍል በማብቃት ተቋማቸው እና ሀገራቸው የጣሉባቸውን ተልዕኮዎች ለመፈጸም ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በዝግጅቱ ላይ የምዕራብ እዝ ኦርኬስትራ ለታዳሚው አዝናኝ ዝግጅቶችን አቅርቧል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
