
ባሕር ዳር: የካቲት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን የማጠቃለያ መርሐ ግብር ምክንያት በማድረግ በማርሽ ባንድ የታገዘ የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሂዷል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ ሴቶች ጤናቸውን ጠብቀው እና ከድባቴ ወጥተው በሁሉም መስክ ውጤታማ እንዲኾኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
ቀኑን በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ስናከብረውም ሴቶች የዚህ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ታስቦ ነው ብለዋል።
ምርጫ ለማድረግ የመራጮች ምዝገባ መጀመሩን የጠቀሱት ኀላፊዋ ሴቶች ተመዝግበው በምርጫው በንቃት መሳተፍ እንዳላባቸው አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዝና ጌታቸው የሴቶች ቀን በተለያዩ ሁነቶች ሲከበር መቆየቱን ተናግረዋል። ተግባራቱ የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያርጋግጡ ናቸው ብለዋል።
የኮሪደር ልማትን ተከትሎ ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ የተፈጠሩ ምቹ አጋጣሚዎች በመጠቀም ማኅበረሰቡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ራሱን ከበሽታ እንዲከላከል ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ሴቶች ጤናማ ሲኾኑ ቤተሰብ ሰላም ይኾናል፤ ሴቶች ከቤት ወጥተው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ እና በመመርመር ጤናቸውን መጠበቅ የዘወትር ተግባር ሊያደርጉት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የተያዙ ተግባራት ተከናውነው በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉን ገልጸዋል።
በምክትል ርእሠ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በዓሉን ስናከብር ቀደምት እናቶቻችን የሠሩትን በጎ ሥራ የምናወድስበት እና እኛም የእነሱን ፈለግ ተከትለን በጎ የምንሠራበት ሊኾን ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በርካታ ጀግና ሴቶች እንደነበሩ አንስተዋል። ዓደዋ ሲነሳ እቴጌ ጣይቱ ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፤ ድሉ ያለ እርሳቸው አይታሰብም ነበር ብለዋል።
አሁን ላይም በሁሉም ዘርፍ ጀግና ሴቶች አሉ ያሉት አሥተባባሪዋ ነገር ግን በቂ አደለም “ብዙ ጀግና ሴቶችን ማፍራት እና የሴቶች መብት እንዲከበር እና እኩልነት እንዲረጋገጥ መሥራት ያስፈልጋል” ብለዋል።
አሁንም የሥራ ጫና ያለባቸው ከቤት ያልወጡ ሴቶች እንደሚገኙ ጠቁመዋል። እነዚህን ሴቶች እንደ አቅማቸው እንዲሠሩ ለማድረግ መሠራት ይገባል ብለዋል። አንድነት፣ መተባበር እና መከባበር ካለ የማናሳከው ድል፤ የማናልፈው ችግር አይኖርም ነው ያሉት።
ነጻ የኾነች ሴት ልትኖር ይገባል ያሉት አሥተባባሪዋ
ሴቶች ከጾታዊ ጥቃት ነጻ እንዲኾኑ መሥራት ይገባል ብለዋል። ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ጤናን መጠበቅ እንደሚገባም መክረዋል።
በውድድሩ አሸናፊ የኾኑ ሴት ተወዳዳሪዎች የገንዘብ እና የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
