
ወልድያ: የካቲት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን ራያ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያሳለፈውን ውሳኔ የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
በቆቦ ከተማ በተካሄደው ሰልፍ የራያ አላማጣ፣ የራያ ባላ፣ የዛታ፣ የኦፍላ ወረዳዎች፣ የአላማጣ ከተማ እና የኮረም ከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
ሰልፈኞቹ ማንነት ድርድር እንደማይደረግበት ገልጸዋል። እኛ ጥያቄያችን የማንነት ነው፤ እነሱ ደግሞ የመሬት ነው፤ የማንነት እና የመምረጥ መብት ደግሞ በመሬት ፈላጊዎች እንዲደናቀፍ መፍቀድ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብትን መንፈግ ነው ብለዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የምርጫ ቦርድ የመምረጥ መብታቸው እንዲከበር በወሰኑት ውሳኔ ደስተኞች መኾናቸውን ገልጸዋል። ለተግባራዊነቱም ከመንግሥት ጎን እንቆማለን ብለዋል።
የወሎ ራያ አማራ የማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ መንገሻ ቸሩ ከትግራይ ክልል ውጭ በመኾን አካባቢዎቹ ምርጫ እንዲያደርጉ የተወሰነውን ውሳኔ ለራያ አማራ ሕዝብ ተግቢ እና ትክክለኛ ውሳኔ መኾኑን ገልጸዋል።
የመምረጥ እና የመመረጥ መብት በኤፌዴሪ ሕገመንግሥት በግልጽ የተደነገገ መብት መኾኑን አንስተዋል።
በተወሰነው ውሳኔ ተቃውሞ የሚያሳሙ አካላት የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት የሚነጥቅ፣ ማንነትን የሚደፈጥጥ ኢ ፍትሐዊ ተግባር በመኾኑ የወሎ፣ ራያ፣ ወፍላ ሕዝብ ተግባሩን ከልብ ያወግዛል ብለዋል።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠውን ውሳኔ መሠረት በማድረግ በምርጫ ቦርድ ይፋ የተደረገውን ውሳኔ የሕዝብን የዘመናት ጥያቄን መሠረት ያደረገ፣ በሕዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን የተወሰደ በጎ እና ፍትሐዊ ውሳኔ መኾኑን ገልጸዋል። ውሳኔውን እናክብራለን፤ እናስከብራለን፤ ለተግባራዊነቱም በቁርጠኝነት እንሠራለን ነው ያሉት።
በተወሰነው ውሳኔ ደስታቸውን ለመግለጽ እና ውሳኔውን ለመደገፍ ሰልፍ መውጣታቸውንም አንስተዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ተወካይ እና የዞኑ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ሞላ ደሱ የራያ አማራ ሕዝብ ለዓመታት ያደረገውን የነፃነት ትግል መንግሥት ይደግፋል ብለዋል።
በዴሞክራሲያዊ መንገድ ጥያቄው መልስ እስከሚያገኝ ድረስ የዞኑ እና የክልሉ መንግሥት ድጋፉን ይቀጥላል ነው ያሉት። ጥያቄው እስኪመለስ ድረስ ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጋር እንዲቆምም ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
