“የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሴቶች ሚና ከፍተኛ ነው ” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

10

ደሴ: የካቲት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ በዓለም 115ኛ በኢትዮጵያ ለ50ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን”50 ዓመት የሴቶች ድምጽ ለዕኩልነት እና ለበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ መልዕክት አክብሯል።

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሴቶች ሚና ከፍተኛ በመኾኑ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዘርፍ የሴቶችን ንቁ ተሳትፎ ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።

ዕኩልነትን ከንግግር ባለፈ በተግባር ማረጋገጥ ያስፈልጋል፣ ለዚህም ከሴቶች በኩል የአመለካከት መዛነፍን ማስተካከል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ትውልድ ለመቅረጽ፣ ጤናማ ቤተሰብ ለመፍጠር፣ ሰላምን ለማረጋገጥ ሴቶች ትልቅ ኀላፊነት አለብን ነው ያሉት።

ምርጫው ሰላማዊ ፣ አሳታፊ፣ ነፃ እና ፍትሐዊ እንዲኾን ሴቶች በንቃት መሳተፍ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ትዕግሥት አበበ በዓሉ ከየካቲት አንድ ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር መቆየቱን ገልጸዋል።

በከተማዋ የሴቶች ተጠቃሚነት እያደገ ቢመጣም አሁንም ቀሪ ሥራዎች አሉ ያሉት ኀላፊዋ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አሚኮ ያነጋገራቸው የበዓሉ ታዳሚ ሴቶች ባለፉት 50 ዓመታት የሴቶች ተጠቃሚነት እና ዕኩልነት እንዲጎለብት በተሠሩ ሥራዎች ሴቶች ተጠቃሚ መኾን ችለናል ብለዋል።

“ነገር ግን አሁንም የማኅበረሰቡ ግማሽ አካል እንደመኾናችን በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊ እና በሌሎችም ዘርፎች ለዕኩል ተጠቃሚነት መታገል ይገባናል” ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ከድር አሊ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሴቶች የማሕጸን በር ጫፍ ካንሰር በመመርመር ራሳቸውን ማወቅ እና ጤናቸውን መጠበቅ አለባቸው።
Next articleአስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም በመገንባት ለሌሎች ሥራዎች አስቻይ ሁኔታን መፍጠር ይገባል።