
ባሕር ዳር፡ የካቲት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “50 ዓመታት የሴቶች ድምፅ ለእኩልነት እና ለበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ መልዕክት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በጎንደር ከተማ በጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር እና በልዩ ልዩ ኹነቶች ተከብሯል።
የሴቶችን ቀን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ115ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ ነው እየተከበረ የሚገኘው።
በሩጫ ውድድሩ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ሕፃናት ተሳታፊ ኾነዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሙሉቀን አበበ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ከየካቲት 01 ጀምሮ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር፣ በዲጅታል መታወቂያ ምዝገባ፣ በማህጸን ጫፍ ካንሰር ምርመራ እና በሌሎችም ኹነቶች ሲከበር መቆየቱን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ሴቶች ላይ መሥራት ሀገር ላይ መሥራት ነው ብለዋል። የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ለጤናማ እናትነት እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል ።
ብድር በማመቻቸት፣ ሥልጠናዎችን በመስጠት እና የገቢያ ትስስርን በመፍጠር ሴቶች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል።
የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጋራ መሥራት እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ቃልኪዳን ኃይሌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
