
ባሕር ዳር: የካቲት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “የመደመር መንግሥት እና የሃይማኖት ተቋማት ሚና” በሚል መሪ መልዕክት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች ጋር በባሕር ዳር ከተማ ምክክር እየተደረገ ነው።
በውይይቱ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ ለሰላም፣ ለአንድነት እና ለማኅበራዊ መረጋጋት ከፍተኛ ሥራ በመሥራት ትታወቃለች ብለዋል።
ቤተ ክርስትያኗ ታሪክ በመሥራት፣ ቅርስን በመጠበቅ፣ መልካም ሥነ ምግባርን በመገንባትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተች ትገኛለች ነው ያሉት። የኢትዮጵያን ማንነት የሚገልጹ ጠንካራ ሰነዶችንም ጠብቃ ያቆየች መኾኗን ገልጸዋል።
በሀገረ መንግሥት ምሥረታም ኢትዮጵያውያን ስለ ሀገራቸው የጋራ ግንዛቤ እንዲይዙ፣ ብዝኀ ማንነት ተከብሮ እንዲዘልቅ፣ የሀገር ሰላም እንዲጸና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቷን ገልጸዋል። የሀገር አንድነት እና ትስስር እንዲጠነክር፣ የማኅበራዊ ስምምነት እንዲመጣ የራሷን ድርሻ ስትወጣ መቆየቷንም አንስተዋል።
የቀደመ ታሪኳን እና አበርክቶዋን በመጠቀም በአሁኑ ወቅት እየታዩ ላሉት ችግሮች መፍትሔ በማምጣት በኩል ከቤተክርስቲያኗ የሚጠበቀውን ኀላፊነት ለመወጣት አጠናክራ እንድትቀጥል አሳስበዋል።
የሀገርን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ እና ወደ ግጭት የሚያመሩ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ከመንግሥት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) የመደመር መንግሥት ማንኛውም አለመግባባቶች እና ልዩነቶች በውይይት እና በሰላማዊ መንገድ ብቻ መፈታት እንዳለባቸው ያምናል ብለዋል።
የሃይማኖቱ አባቶችም መንግሥት ለሚያከናውናቸው የዘላቂ ሰላም ግንባታ እና የልማት ሥራዎችም ከመንግሥት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸው አንስተዋል።
ባለፉት ቀናት ከእስልምና፣ ከካቶሊክ፣ ከወንጌላውያን እና ከ7ቀን አድቬንቲስት መሪዎች ጋር ተመሳሳይ ምክክር መደረጉ የሚታወስ ነው።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
