
ደብረብርሃን: የካቲት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ መሪዎች በሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላ እና ጠራ ወረዳ በኅብረት እና በተናጠል በተለዩ ቀበሌዎች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ሞዴል እማወራ ሴቶችን ጎብኝተዋል፡፡
ጎብኝት ከተደረገባቸው መካከል በወረዳው በጨኪ ቀበሌ ነዋሪ የኾነችው ትዕግስት ግርማ ሕይወቷን ለመቀየር ወደ ዓረብ ሀገር ተሰዳ እንደነበር ገልጻለች፡፡ ይሁን እና ከረጅም የስደት ቆይታ በኋላ ወደ ተወለደችበት አካባቢ ተመልሳ በወተት ላም እርባታ ላይ ተሰማርታለች።
በአሁኑ ወቅት ሦሥት የወተት ላሞች ያሏት ሲኾን በቀን 45 ሊትር ወተት ለተጠቃሚዎች እንደምታስረክብ እና በዚህም የተሻለ ኑሮ እየመራች መኾኑን ተናግራለች፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ሰዓዳ ኢብራሂም በዞኑ ሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር በመሪነት ላይም ጉልህ ድርሻ እንዲኖራቸው ሰፊ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
ይሁን እና ሴቶች በሁሉም ዘርፍ የሚገባቸውን ቦታ እንዲያገኙ እና ተጠቃሚ እንዲኾኑ ተደራጅተው መታገል እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን የሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ የሮምነሽ ጋሻውጠና አንጎለላ እና ጠራ ወረዳ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አኳያ ሰፊ ርቀት መሄዱን ጠቅሰዋል።
በተለይ የሴቶችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ሰፊ ተሞክሮ የሚወሰድበት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ተሞክሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የማስፋት ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አትክልት አሳቤ በበኩላቸው የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ሁለንተናዊ ዕድገት መፍጠር መኾኑን የአንጎለላ እና ጠራ ወረዳ ውጤት ማሳያ ነው ብለዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን(አሚኮ) ምክትል ሥራ አሥፈጻሚ ሕሊና መብራቱ የሴቶችን ተጠቃሚነት መሬት ላይ በማውረድ በኩል አመርቂ ሥራ ማየታቸውን ገልጸዋል።
አካባቢው ብዙ ሴት መሪዎች ያሉበት ቢኾንም ከዚህም በላይ የሴቶችን መሪነት ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡
በተለይም የሴቶች ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ሴቶች ለሰላም ያላቸውን አበርክቶ በመጠቀም በጫካ ያሉ ወንድሞችን ወደ ሰላም እንዲመለሱ እና ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ መሥራት አለባቸው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ወንዲፍራ ዘውዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
