ብሎክቼይን – በዲጂታሉ ዓለም የማይናወጥ ዕምነትን መገንቢያ መሣሪያ

53

 

ባሕር ዳር፡ የካቲት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የሳይበር ዓለም ላይ የሚደረግ ማንኛውም የምናባዊ ገንዘብ ልውውጥ ተግባራዊ የሚደረገው ጠንካራ እና ያልተማከለ ሥርዓት ባለው የልውውጥ ስልት ነው፡፡ ይህ ልውውጥ ብሎክቼይን በሚባል ዲጂታል መዝገብ ይሳለጣል፡፡
እንደ አይ.ቢ.ኤም ድረ ገጽ ገለጻ ብሎክቼይን በአንድ ማዕከላዊ የቁጥጥር ሥርዓት ያልወደቀ መረጃዎች በብዙ ኮምፒውተሮች ላይ ተሰራጭተው የሚመዘገቡበት እና አንዴ ከተመዘገቡ በኋላ ሊሰረዙ ወይም ሊቀየሩ የማይችሉበት ዲጂታል የሒሳብ መዝገብ ነው።

ይህ ቴክኖሎጂ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2008 ዓ.ም ሳቶሺ ናካሞቶ በሚባል በይፋ ማንነቱ በማይታወቅ ግለሰብ/ቡድን አማካኝነት ከቢትኮይን (ምናባዊ ገንዘብ) ጋር አብሮ የተዋወቀ ቢኾንም ዛሬ ግን ከዲጂታል የገንዘብ ሥርዓትነት ባለፈ ለጤና ጥበቃ፣ ለንብረት አሥተዳደር እና ለምርጫ ሥርዓቶች እንደ ትልቅ አማራጭ እየታየ ይገኛል።

የብሎክቼይን ዋነኛ ጠቀሜታ እንደ ባንክ ያሉ ማዕከላዊ የቁጥጥር አሠራር ያላቸው ተቋማት ሳይኖሩ በሁለት ወገኖች መካከል የሚደረግን የምናባዊ ገንዘብ ልውውጥ በከፍተኛ ዕምነት አና ግልጽነት ማከናወን ማስቻሉ እንደኾነ አይ.ቢ.ኤም ያስረዳል።

እያንዳንዱ ግብይት እንደ አንድ ብሎክ (የተወሰኑ የግብይት መረጃዎችን/ትራንዛክሽን የያዘ ማኅደር) ተመዝግቦ ከቀዳሚው ጋር በምስጢራዊ ኮድ ስለሚተሳሰር አንዱን መረጃ ለመቀየር መሞከር ሙሉ ሰንሰለቱን ስለሚበጥስ ማጭበርበርን የማይታሰብ ያደርገዋል። ይህ መዋቅር የመረጃን ትክክለኛነት በማረጋገጥ ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው መኾኑንም ገጹ ያስረዳል።

በብሎክቼይን ዓለም ውስጥ እንደ ስማርት ኮንትራት ያሉ በራሳቸው የሚተገበሩ ዲጂታል ውሎች ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። እነዚህ ውሎች አስቀድሞ የተስማሙባቸው ኹኔታዎች ሲሟሉ ወዲያውኑ ተግባራዊ የሚኾኑ በመኾናቸው የንግድ ሥራዎችን ቅልጥፍና ይጨምራሉ።

ለምሳሌ በሸቀጦች ዝውውር ወቅት አንድ ምርት ከየት እንደመጣና የት ደረጃ ላይ እንዳለ በግልጽ ለመከታተል ያስችላል። ይህም በፋይናንስ ሥርዓት ላይ የሚኖርን የማጭበርበር ዕድል በከፍተኛ ኹኔታ ይቀንሳል።

አይ.ቢ.ኤም “ስታቲስታ” የተሰኘውን የጀርመን ድረ ገጽ ዋቢ በማድረግ ያሰፈረው መረጃ የብሎክቼይን ገበያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር እስከ 2032 ዓ.ም ድረስ በአንድ ትሪሊዮን ዶላር እንደሚያድግ እና ይህም የዓለምን የኢኮኖሚ ሥርዓት የመቀየር ትልቅ አቅም እንዳለው ማሳያ ነው።

ቴክኖሎጂው አሁን ላይ ከሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ከነገራተ ኢንተርኔት ጋር በመቀናጀት ይበልጥ እየዘመነ ይገኛል። ይህ ጥምረት መረጃዎችን ይበልጥ ግልጽ እና ደኅንነታቸው የተጠበቀ በማድረግ ለተቋማትም ኾነ ለግለሰቦች አስተማማኝ አሠራርን ይፈጥራል።

የአይ.ቢ.ኤም መረጃ እንደሚያመለክተው ብሎክቼይን መረጃን የማከማቻ ሥርዓት ብቻ ሳይኾን በዲጂታሉ ዓለም ውስጥ የማይናወጥ ዕምነትን መገንቢያ መሣሪያ ነው። ቴክኖሎጂው እያደገ ሲመጣ የንግድ ሥራዎችን ቅልጥፍና ከመጨመር ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግልጽነት የሰፈነበት እና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ይህ አዲስ የቴክኖሎጂ ውጤት ለቀጣዩ ዘመን የንግድ ሥርዓት ዋነኛ መሠረት እንደሚኾንም ይጠበቃል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቴክኖሎጂ የምርጫ ሂደቱን እያቀለለው ነው።
Next articleጦርነትን በማውገዝ ሰላም እንዲመጣ ማድረግ ከንግዱ ማኅበረሰብ ይጠበቃል።