
ባሕር ዳር: የካቲት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባደጉት ሀገራት ምርጫን በዲጂታል ማካሄድ የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ምርጫን በዲጂታል ማካሄድ ካሉት ጠቀሜታዎች መካከል ፍጥነት፣ ውጤታማነት፣ ጊዜ እና ወጭን መቀነስ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ምርጫ ላይ ቴክኖሎጂን መጠቀም በዓለማችን ላይ ፈጣን እና ቀልጣፋ አሠራርን ለመዘርጋት በሚጥሩ ሀገራት ትኩረት እየሳበ የመጣ ጉዳይ ነው። ኾኖም የየሀገራቱ ተሞክሮ እንደየቴክኖሎጂ አቅማቸው እና እንደ ፖለቲካዊ ሁኔታቸው ይለያያል።
ቴክኖሎጅን ለምርጫ ከሚጠቀሙ ሀገራት መካከል ብራዚል እና ህንድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ የሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በዲጂታል ቴክኖሎጅ የታገዘ እንደሚኾን ተነግሯል፡፡
👉 ለመኾኑ ምርጫውን በምን መልኩ ነው በዲጂታል ለማገዝ የታሰበው?
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኀይሉ ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅቱ ቀደም ብሎ መጀመሩን አንስተዋል። ለምርጫው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ላይ ለማዋል ጥናት ተደርጎ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡
የመራጮችን እና እጩዎችን ምዝገባ ዲጂታላይዝድ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ የመራጮችን እና የዕጩዎችን ምዝገባ በቴክኖሎጅ ለማድረግ የሕግ ድጋፍ የሚያስፈልገው በመኾኑ የምርጫ ቦርድ ሕጎችን በማሻሻል ሥራዎችን እንደሠራም ጠቁመዋል፡፡
የመራጮችን እና የዕጩዎችን ምዝገባ በቴክኖሎጅ መደገፍ ምርጫውን የተሻለ ፍትሐዊ እና ገለልተኛ ለማድረግ ይጠቅማል ነው ያሉት፡፡ ለአብነትም የዕጩዎች ምዝገባ በቴክኖሎጂ መታገዙ ዕጩዎች በምርጫ ጣቢያዎች ለምዝገባ ሲሄዱ ይቀርቡ የነበሩ ችግሮችን ፈትቷል ነው ያሉት፡፡
ዕጩዎች ባሉበት ቦታ ኾነው መመዝገባቸው ከገለልተኝነት አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበረው አንስተዋል፡፡ ሥራውንም ቀልጣፋ እና በሰዓት ያልተገደበ እንዳደረገውም ገልጸዋል፡፡
የመራጮች ምዝገባም በዲጂታላይዜሽን እንደሚደረግ ነው የገለጹት፡፡ ማንም ሰው በቤቱ ኾኖ ስማርት ስልክ በመጠቀም ራሱን በመራጭነት መመዝገብ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ይህም አካል ጉዳተኞችን ወደ ምርጫ ጣቢያ መሄድ የማይችሉትን እና ባሉበት ኾነው መመዝገብ የሚፈልጉትን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ቅዳሜ የካቲት 28 ጀምሮ የመራጮች ምዝገባ ይጀምራል፤ ስማርት ስልክ በመጠቀም እና ‘ምርጫዬ’ የተሰኘችውን የሞባይል መተግበሪያ (አፕሊኬሽን) በስልክ ላይ በማውረድ ማንኛውም ሰው በቤቱ ቁጭ ብሎ ራሱን እና ቤተሰቦቹን ለመመዝገብ በሚያስችለው ሲስተም መመዝገብ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡
ለዓይነ ስውራንም ሲስተሙ በድምጽ የሚመራ በመኾኑ ራሳቸውን ለመመዝገብ እንደሚያስችላቸው ነው የገለጹት፡፡ ይህም አካታችነትን የሚያቀላጥፍ ነው ብለዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን በምርጫ ጣቢያ ላይ በምርጫ ቦርድ ሠራተኞች በታብሌት በታገዘ እና ዲጂታላይዜሽንን በመጠቀም የመራጮች ምዝገባ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡ ይህም የምርጫን ቴክኖሎጂ በትንሹ ለመጀመር የታሰበ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ካለው የመሰረተ ልማት አንጻር ዲጂታላይዜሽን ተግባራዊ የሚደረገው ካሉት 45 ሺህ በላይ የምርጫ ጣቢያዎች መካከል በ17 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ብቻ ነው ብለዋል። በተለይም ደግሞ ከሦስተኛው ትውልድ ( 3ጂ) በላይ የኢንተርኔት አገልግሎት ባሉባቸው አካባቢዎች ይተገበራል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
