
ባሕር ዳር፡ የካቲት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር “ለሰላም ዘብ እንቆማለን፤ የልማት አርበኛ እንኾናለን” በሚል መሪ መልዕክት ከንግዱ ማኅበረሰብ እና ከባለሃብቶች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ዓለም አሁን ላይ በተለያዩ ችግሮች እየታመሰ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ደግሞ በዓለም ላይ በሚፈጠሩ ችግሮች ብቻ ሳይኾን በአፍሪካ ቀንድ የቀይ ባሕር የጂኦ ፖለቲካ ተዋናይ ሀገር መኾኗን አንስተዋል። የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እና የአፍሪካውያን ድምጾች የሚሰሙባት ወሳኝ ሀገር በመኾኗ የዓለም ፖለቲካ ችግሮች እና በጎ ውጤቶችን የምትቀምስ ሀገር መኾኗን አንስተዋል።
ባዕዳን ባንዳዎችን ተጠቅመው ጥቃቅን የውስጥ ችግሮችን በማጉላት ሀገራችን ላይ ከፍተኛ ችግር የማድረስ እና ሰላሟ ላይ ስጋት የመደቀን ፍላጎት እያሳዩ መኾናቸውን ገልጸዋል። የሰላም ጠንቅ፣ የልማት ጎታች የኾኑትን እነዚህን ኀይሎችም ሁሉም ሊታገላቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።
የጦርነት ትርፉ የሰው ሕይወት ማጣት እና ንብረት ማውደም መኾኑን የሚረዳው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ሰላም ወዳድ፣ ልማት እና መልካም አሥተዳደር ፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል።
የውስጥ የጽንፈኝነት እንቅስቃሴን፣ የውጭ ጠላትን መታገል እና ሰላምን ማስፈን ከንግዱ ማኅበረሰብ የሚጠበቅ ነው ብለዋል።
ከተማዋ በተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንደምትገኝ ተናግረዋል። የኮሪደር ልማት ሦሥተኛ ዙር ሥራም እየተፋጠነ መኾኑን ጠቅሰዋል። እነዚህን የልማት ተግባራት ለማጠናቀቅ እና አጠናክሮ ለማስቀጠል የገቢ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በዚህ ዓመት ከታቀደው 10 ቢሊዮን ብር ገቢ ውስጥ እስካሁን 5 ነጥብ 25 ቢሊዮን መሠብሠቡን የጠቆሙት ምክትል ከንቲባው ይህም ለሰላም ለተደረገው ጥረት የከተማዋ ነዋሪ የከፈለው ዋጋ ነው ብለዋል።
የከተማዋን ሰላም እና ልማት እውን ለማድረግ ነጋዴው ማኅበረሰብም ኾነ ነዋሪዎች ለሚያደርጉት ድጋፍ ከተማ አሥተዳደሩ ምሥጋና እንዳለው ተናግረዋል።
መድረኩ የተቋማዊ ሥራዎችን፣ የልማት፣ የሰላም ሥራዎችን፣ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን በመገንዘብ ዝግጁ መኾን እንዲቻል የሚካሄድ መኾኑንም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
