” የሃይማኖት ተቋማት ለሰላም፣ ለሕዝብ አንድነት እና ለሀገር ግንባታ ሚናቸው የላቀ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

25

 

ባሕር ዳር፡ የካቲት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “በመደመር መንግሥት የሃይማኖት መሪዎች ሚና” በሚል መሪ መልዕክት ከወንጌላውያን አማኞች፣ ከ7ኛ ቀን አድቬንቲስት እና ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን የሃይማኖት መሪዎች ጋር በባሕር ዳር ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የተውጣጡ የየሃይማኖቶቹ አባቶች ተገኝተዋል።

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የሃይማኖት ተቋማት ለሰላም እና ለሕዝብ አንድነት የላቀ ሚና አላቸው ብለዋል። ለማኅበራዊ መረጋጋት፣ ለሀገር ግንባታ እና እሴትን በመጠበቅ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ጠንካራ ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛ አበርክቶ እንዳላቸው ያመላከቱት ርእሰ መሥተዳደሩ ሰላምን በመጠበቅ በኩልም ትልቅ ኀላፊነት እንዳለባቸው አንስተዋል።

የሃይማኖት መሪዎችም ለችግሩ የመፍትሔው አካል በመኾን ሰላምን ለማጽናት በሚደረገው ጥረት ከመንግሥት ጋር በመተባበር ኀላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

በተለይም አሁን ያጋጠመው የሰላም እጦት የሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ፣ የመንግሥት እና የሕዝብን ሃብት እያወደመ በመኾኑ ችግሮችን ለመፍታት በአንድነት መቆም ይገባል ብለዋል። በሃይማኖቶች መካከልም ተቀራርቦ መሥራት እና መተባበር እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

የሃይማኖት መሪዎች በየቤተ እምነቶቻቸው በማስተማር እና በመስበክ በኩል ጠንካራ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። የሃይማኖት ተቋማትም እርስ በእርሳቸው ትስስርን በመፍጠር ተከታዮቻቸውን ማስተማር ይገባቸዋል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) መንግሥት ለሚያከናውናቸው የሰላም እና የልማት ሥራዎች የሃይማኖት ተቋማትም ተቀራርበው በጋራ መሥራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

በሃይማኖት ተቋማት በኩል አንድነትን፣ መግባባትን፣ መሠባሠብን እና እኛነትን በማስቀደም በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል። የሀገር እና የሕዝብን ሰላም ከሚያውኩ፣ ልማትንም ከሚያደናቅፉ አስተሳሰቦች መራቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበቃብትያ ሁመራ ወረዳ ሕዝባዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።
Next articleየሰላም ጠንቅ እና የልማት ጎታች የኾኑ ኀይሎችን መታገል ይገባል።