
ባሕር ዳር፡ የካቲት 27/2018 (አሚኮ) ለአንድ ሀገር የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች የሀገራት የቀደመ ታሪክ ወሳኝነት አለው። በተለይም የዓድዋ ድልን የመሰሳሉ የታሪክ ክስተቶች ለዲፕሎማሲ ከፍ ያለ ተጽዕኖ አላቸው።
የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ በጦርነት የማሸነፍ ወታደራዊ ድል ብቻ ሳይኾን በዓለም አቀፍ መድረክ ሉዓላዊነቷ እንዲከበር፣ የዲፕሎማሲ አድማሷ እንዲሰፋ ያስቻለ የታሪክ ምዕራፍ ነው። የዓድዋ ድል ከነጻነት ባሻገር ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በር የከፈተ፣ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተቀባይነቷን ከፍ ያደረገ አንዱ የታሪክ ክስተት ስለመኾኑም ታሪክ ያስረዳል።
በጅንካ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ተስፋዬ ገብረማርያም እንደገለጹት የዓድዋ ድል ነጮች ለጥቁር ሕዝቦች የነበራቸውን የተሳሳተ አመለካከት ቀይሯል። ምዕራባውያን በአፍሪካ ላይ የነበራቸውን ተጽዕኖ ቆም ብለው እንዲያስቡ ያስገደደ ክስተትም ነው።
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ከፍ ያለ የዲፕሎማሲ ተቀባይነት እንድታገኝ ምቹ አጋጣሚ የፈጠረ መኾኑንም የታሪክ መምህሩ ያስረዳሉ። ከዓድዋ ድል ማግሥት ጣሊያን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ እና ሩሲያን የመሳሰሉ ሀገራት በአዲስ አበባ ኤምባሲዎቻቸውን መክፈታቸው እና ቀጥተኛ ግንኙነት መመሥረታቸው በማሳያነት አንስተዋል።
እንደ መምህሩ ማብራሪያ በዓለም ዓቀፍ መድረኮች ተሰሚነቷ እንዲጨምር፣ በተለያዩ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችም በአባልነት እንድትሳተፍ ዕድል ፈጥሮላታል። በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በሚደረጉ ስምሪቶች ሳይቀር ተፈላጊ እንድትኾንም አስችሏታል።
ኢትዮጵያ በዓድዋ የተጎናጸፈችው ድል አፍሪካውያንም ወደ አንድ ጥላ ስር እንዲሠባሠቡ፣ የጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግልን አጠናክረው እንዲቀጥሉ በር ከፍቷል ብለዋል። ለፓን አፍሪካኒዝም እና ለተለያዩ የነፃነት ንቅናቄዎችም መነሻ ኾኗል።
የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረትን ለመመሥረት በነበረው እንቅስቃሴ ተሰሚነት እንዲኖራት ድርሻው የጎላ ነበር ይላሉ። የኅብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ እንዲኾን ካስቻሉ አሳማኝ የታሪክ አስረጅዎች መካከል አንዱ የዓድዋ ድል ያስገኘው የሞራል የበላይነት ነበር። ይህም ኢትዮጵያ በአፍሪካውያን ዘንድ ተሰሚነት እንዲኖራት አስችሏል ነው የሚሉት።
ድሉ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ቀንበር ሳይወድቁ በራስ የመተማመን መንፈስ የዲፕሎማሲ መስመሯን እንድትቀይስ አስችሏታል።
የአሁኑ ትውልድም ከዓድዋ ድል ታሪክ ትምህርት በመውሰድ ብሔራዊ ጥቅምን በጋራ የመጠበቅ፣ ወዳጅ ሀገራትን የማብዛት እና በዲፕሎማሲው የበላይነትን የመያዝ ኀላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
