
ባሕር ዳር: የካቲት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ቀን ተቆርጦለት እና መርሐ ግብር ወጥቶለት ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት በሥራ ላይ ናቸው፡፡
ፖለቲካ ፓርቲዎች ስትራቴጂ እና ፕሮግራማቸውን እያስተዋወቁ ነው፡፡ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ባላቸው ልዩነት እና አንድነትም መከራከር ጀምረዋል፡፡ ምርጫ ቦርድም በበኩሉ ተወዳዳሪዎችን በመመዝገብ እና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን በመሥራት ላይ ነው፡፡
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዋ ወይዘሮ መብራት ፈለቀ ዘንድሮ በሚደረገው ምርጫ ለመሳተፍ እየጠበቁ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በአካባቢያቸው ለምርጫው ቅስቀሳ እየተደረገ እና በየአደረጃጀቱ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ምርጫ ሕዝቡ ይመራኛል የሚለውን መንግሥት የሚመርጥበት ነው ያሉት ወይዘሮ መብራት ለመምረጥ በዝግጅት ላይ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ዕድሜው ለምርጫ የደረሰ ሁሉ መሳተፍ እንዳለበትም ነው የመከሩት፡፡
በመራጭነት ተመዝግቦ ካርድ መውሰው ቀድሞ መደረግ ያለበት ዝግጅት እንደኾነም ገልጸዋል፡፡
ግጭቶች ቢኖሩም በአንድ በኩል ለሰላም እየሠሩ በሌላ በኩል ምርጫን የማካሄድን ተገቢነት አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ስለዘንድሮው የምርጫ ሂደት ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ ምርጫውን በአግባቡ ለማከናወን ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ሕዝብ መብቱ በእጁ መኾኑን በማመን የሚመሩትን ሰዎች ራሱ መወሰን አለበት። ምርጫ ሂደት ስለኾነ በአንድ ጊዜ የተሟላ እንደማይኾን ወይዘሮ ሜላትወርቅ ገልጸዋል፡፡ የኔ ድምጽ ለውጥ አያመጣም በሚል ማመንታት አይገባም ብለዋል፡፡ በማመንታት ያልመረጠ ሰው ሌላው በመረጠው ሰው እንደሚተዳደር ተናግረዋል፡፡
ምርጫ የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ እና ትብብር እንደሚፈልግ አንስተዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ማስተማር እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
ምርጫውን አካታች እና አሳታፊ ለማድግ ምርጫ ጣቢያዎችን በመጎብኘት እና በማጥናት ተሠርቷል። ለሴቶች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለአረጋውያን ምቹ መኾናቸውን ተፈትሿል ነው ያሉት፡፡ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችም በምርጫ የሚሳተፉበት መንገድ ተጠንቶ ለፖሊሲ አውጭዎች ተልኳል ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከመንግሥት የሚሰጣቸውን በጀት ለአካታችነት እንዲጠቀሙበት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። ይህንኑም የሀገር ውስጥ እና የውጭ ታዛቢዎች እንደሚከታተሉትም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
