ካራማራ የኢትዮጵያዊነት ማኅተም።

18
ባሕር ዳር፡ የካቲት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ክብር ለመድፈር የተነሱ ወራሪዎች ሁሉ የኢትዮጵያውያንን የማይበገር ክንድ ቀምሰው ተመልሰዋል። ከእነዚህም መካከል “በታላቋ ሶማሊያ ምስረታ” ሕልም የሰከረው እና የኢትዮጵያን ምድር ለዓመታት ሲመኝ የነበረው የዚያድ ባሬ ወራሪ ኀይል አንዱ ነበር።
ወራሪው ዚያድ ባሬ በ1953 ዓ.ም እና በ1956 ዓ.ም ድንበር ተሻግሮ የኀይል ወረራ ሙከራዎች ቢፈጽምም በኢትዮጵያ ሠራዊት ተመትቶ ተመልሷል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ግን መልካም አጋጣሚ እስኪፈጠርለት ድረስ መጠባበቅን ነበር የመረጠው። በ1969 ዓ.ም የኢትዮጵያን መንግሥት በራሱ ውስጣዊ ችግር የተለያዩ ተቃዋሚዎች በየአካቢው የትጥቅ ትግል በመጀመራቸው እና በሌሎች ምክንያቶች መንግሥት ችግር ውስጥ ወደቀ።
ይህ ወቅት ለዚያድባሬ መንግሥት የተመቻቸ ጊዜ ስለፈጠረለት እስከ አዋሽ ወንዝ ድረስ ያለውን መሬት ለመጠቅለል ቆርጦ ተነሳ።
ከየካቲት/1969 ዓ.ም ጀምሮ በዋርዴር፣ በቀብሪዳሐር፣ በዶገነቡር፣ በጎዴ እና በድሬድዋ ግንባሮች ሰባት ብርጌዶችን በማሰለፍ ወረራ ፈጸመ። እስከ 700 ኪሎ ሜትር ድረስም ዘልቆ መግባት ቻለ።
የወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ወረራውን ለመመከት 300 ሺህ የሚሊሻ ሠራዊት በሦሥት ወር በማሠልጠን በግንባር አሰለፈ። ጦሩ በከፍተኛ እልህ እና ቁጭት እየተፋለመ የካቲት 26/1970 ዓ.ም ካራማራ ላይ የወራሪው የዚያአድባሬ ሠራዊትን አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ ከሀገሪቱ እንዲወጣ አደረገ።
የአሸናፊነቱ ምስጢር፦
የሶማሊያ መንግሥት ከ10 ዓመት በላይ ሲያስታጥቁት የኖሩትን የሶቭየት እና የኪዩባ አማካሪዎች ከሶማሊያ በማባረሩ ከባድ የሚባል የመሣሪያ እጥረት ገጠመው፡፡
የሶማሊያ የኢኮኖሚ እና የሰው ኀይሏ የውጊያ ጥንካሬ ተዳከመ። በአንፃሩ ወረራው ሲጀመር በሰው እና በመሳሪያ ኀይል በእጅጉ ተበልጦ የነበረው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከስድስት ወራት በኋላ ግን በሰው እና በመሣሪያ የበላይነትን መቀዳጀት ቻለ፡፡ በተለይ የተዋጊ የሰው ኀይሏ አጅግ እየጨመረ ሄዶ በጥር 1970 ዓ.ም ሰባት ክፍለ ጦሮች ደረሰ፡፡
የማይበገር የሀገር ፍቅር፦
የኢትዮጵያውያን የአንድነት መንፈስ፣ ጥልቅ የሀገር ፍቅር፣ ለሀገር ክብር የመሞት ጽኑ ፍላጎት፣ የሠራዊት ጠንካራ መከላከል እና መልሶ ማጥቃት ለድሉ በምክንያትነት ይነሳል።
የአየር ኀይሉ ድንቅ ብቃት፦
የኢትዮጵያ አየር ኀይል የሶማሊያ ታንኮችን፣ ብረት ለበሶችን፣ መድፎችን እና ተዋጊ አውሮፕላኖችንም ጭምር በተጠናከረ መንገድ ማውደም ችሏል። ወደ ሶማሊያ ድንበር ዘልቆ በመግባት የአየር ማረፊያዎችን እና የጦር መሳሪያ ማከማቻዎችን ማውደም ቻለ።
የኢትዮጵያ አሸናፊነት ዋነኛው ምስጢር የመንፈስ ልዕልና ነው። እንደ ተራራ የገዘፈ ጽናት፣ እንደ ዓባይ የሚፈስ የሀገር ፍቅር እና እንደ አለት
የጠነከረ አንድነት ውጤት መኾኑ ይነገራል።
በወቅቱ ከተዜሙ ዜማዎች መካከልም፦
ሆ ብየ እመጣለሁ ሆብየ በድል፣
ጥንትም ያባቴ ነው ጠላትን መግደል፣
ሆ ብዬ እመጣለሁ ልበ ሙሉ ጀግና ፍራት የሌለብኝ፣
እኔስ ለኢትዮጵያ ቃልኪዳን አለብኝ፣
ያያት የቅድመ አያት ወኔ ያልተለየኝ፣
ዛሬም ለኢትዮጵያ ታጋይ ተጋዳይ ነኝ፣
ጀግኖች በደማቸው ያቆዩትን ሀገር፣
ዛሬም በልጆቿ ለዘላለም ትኑር፣
ባያት በቅድመ አያት የኖረች ተከብራ፣
አልያት በቁሟ እምየ ተደፍራ፡፡ የሚለው ይጠቀሳል።
በመረጃ ምንጭነት፦
​ኃይለማሪያም ኤፍሬም (2013 ዓ.ም) – የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባሕልና የተፈጥሮ መስህብ።
​ፋንታሁን አየለ (ዶ.ር) – የኢትዮጵያ ሠራዊት ከድል ወደ ውድቀት (ከ1967-1983) እና የተለያዩ ድኅረ ገጾች ተጠቅመናል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!!
Previous articleየኩላሊት ጠጠር በሽታ ምልክት፣ ሕክምና እና መከላከያው
Next articleየሕዝቡ የመምረጥ መብት በእጁ ነው።