የኩላሊት ጠጠር በሽታ ምልክት፣ ሕክምና እና መከላከያው

5
ባሕር ዳር፡ የካቲት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎በሽታው በኩላሊት ክፍል የሚከሠት ጠጠር ሲኾን በሥርዓተ ፍጭት መዛባት ምክንያት የሚከሠት እንደኾነ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ይዘንጋው ይሁን በአሽከርካሪነት ሙያ ላይ የተሰማራ ወጣት ነው። በሥራ ላይ እያለ ከባድ ሕመም ስላጋጠመው ወደ ሆስፒታል አቀና። የሕክምና ባለሙያዎችም ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ የኩላሊት ጠጠር እንዳለበት ይነግሩታል። ከዚያም ችግሩን በሕክምና በመታገዝ ከሕመሙ እንዲያገግም መደረጉን ይገልጻል።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ በሽታው እንደገና ከፍተኛ ደረጃ ደረሰና ቀዶ ሕክምና ተደርጎ ጠጠሩ እንዲወገድ ቢደረግም ሕመሙ አሁንም መኖሩን ተናግሯል። ምክንያቱ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ለአደጋ ዳረገኝ ሕይወቴን አመሰቃቀለው ብሏል ወጣቱ።
ችግሩ ከሕመሙ በላይ የሚያደርሰውን የሥነ ልቦና ጉዳት እና የኢኮኖሚ ቀውስ ሰው ከሚናገረው እና ከሚያወራው በላይ የአዕምሮ ቁስል መኾኑን ከውስጡ እያዘነ ይናገራል።
የኩላሊት ጠጠር ችግር በጣም ከባድ ሕመም ያለው በመኾኑ ሁሉም ሰው በኔ የደረሰ እንዳይደርስባቸሁ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል በማለት ሀሳቡን አጋርቷል።
በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥበበ ግዮን እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኩላሊት እና ፊኛ ኘሮስቴት ሳብ እስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር መኳንንት ይመር የኩላሊት ጠጠር ችግር በአብዛኛው በአምራች ዜጎች ማለትም ከ30 እስከ 50 ዓመት የዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎች ላይ የሚከሰት ችግር እንደኾነ ይገልጻሉ። በብዛት ደግሞ ወንዶች ላይ የሚከሰት ነው ብለዋል።
ችግሩ በተለያዩ መንስኤዎች የሚከሠት ቢኾንም የሚወሰዱ ፈሳሽ ነገሮች እና ምግቦች እንደሚወስኑት ተናግረዋል። በአብዛኛው በሰውነት ውስጥ በቂ ፈሳሽ አለመውሰድ፣ ከመጠን በላይ ጨዉ አብዝቶ መጠቀም፣ ረጅም ጊዜ በሚወሰድ መድኃኒት ማለትም ለግፊት፣ ለኤች አይ ቪ፤ በተጓዳኝ እና በሜታቦሊክ በሽታዎች፣ በሽንት ቧንቧ መዘጋት እና ከኢንፌክሽ በተጨማሪ በሞቃታማ የአየር ሁኔታ መኖር እና በቂ የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግ አጋላጭ ምክንያት ናቸዉ ይላሉ።
የኩላሊት ጠጠር ችግር ምልክት ያለው እና የሌለው እንደሚኖርም ጠቁመዋል። ምልክት ያለው የኩላሊት ጠጠር የጎን ውጋት እና የምኝታ አለመመቸት፣ የሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት እና የማቃጠል ስሜት፣ የሽንት ቀለም መቀየር፣ በሽንጥ በኩል ሕመም መሠማት፣ ማስታወክ፣ ማቅለሽለሽ እና ቁርጠት፣ የሆድ ሕመም ተጠቃሽ ምልክቶች ናቸው ነው ያሉት።
የኩላሊት ጠጠር በመጠን ይለካል፤ ችግሩ ከትንሽ ሕክምና እስከ ቀዶ ሕክምና መኖሩን ያስረዳሉ።
የኩላሊት ጠጠሩ ከ5ሚሊ ሜትር በታች ከኾነ ተጨማሪ ሕክምና የማይፈልግ እና በቂ ፈሳሽ በመውሰድ የሚድን መኾኑን ነው ያስረዱት።
ማንኛውም የኩላሊት ጠጠር በቀዶ ጥገና ይወጣል ማለት እንዳልኾነም አስረድተዋል። ይህም የሚወሰነው እንደ ጠጠሩ መጠን ሲኾን የጠጠሩ መጠን እስከ 10 ሚሊ ሜትር ከኾነ በሽንት እንዲወጣ እንደሚደረግ ነው የተናገሩት።
መጠናቸው ከ10 ሚሊ ሜትር በላይ ከኾነ የመውጣት ዕድሉ ጠባብ ስለኾነ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ይጠበቃል ነው ያሉት።
ለምሳሌ በጨረር በመታገዝ ጠጠሩ እንዲሰባበር በማድረግ ከዛም ውኃ በመጠጣት በሽንት እንዲወጣ ይደረጋል፤ አለፍ ሲልም በቀዶ ጥገና እንዲወጣ ይደረጋል ነው ያሉት።
ነገር ግን የተጎዳውን ኩላሊት መልሶ ማዳን አይቻልም፤ ነገር ግን ችግሩን በአለበት መግታት ነው ብለዋል።
የኩላሊት ጠጠር ካልታከመ ደግሞ ለኢንፌክሽን ከማጋለጡ በተጨማሪ የሽንት ቱቦን በመዝጋት ኩላሊትን ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ እስከማድረስ ሊደርስ ይችላል ብለዋል።
እንደ ዶክተሩ ገለጻ የኩላሊት ጠጠር ችግር ታካሚ ሰዎች ውስጥ ከ10 እስከ 15 ዓመት ባለው ጊዜ 50 በመቶ ሰዎች ተመልሶ በችግሩ የመያዝ ዕድል እንዳላቸዉ ነው የተናገሩት።
ችግሩ አንዴ ከተከሰተ ደጋግሞ የመከሰት ዕድል ስላለው ሰዎች ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ሙያዊ ምክረ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
የኩላሊት ጠጠር ችግርን መከላከል የሚቻለዉ፦
👉የአመጋጋብ ሥርዓትን በማስተካከል
👉የሚጠቀመውን የጨው መጠን መቀነስ
👉መድኃኒቶች በሕክምና ባለ ሙያ ምክር መውሰድ
👉ህመም ሲሰማ በአቅራቢያቸው ወደ ሚገኝ ጤና ተቋም በመሄድ ምርመራ ማድረግ
👉ችግሩ እንዳለበት ከተነገረው የሕክምና ሙያተኛ ምክረ ሀሣብ ተግባራዊ ማድረግ
👉በቂ ፈሳሽ መውሰድ
👉በቂ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለበት ሙያዊ ምክረ ሀሣባቸውን ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!!
Previous articleዓለም አቀፍ የቡና ገበያ ዋጋ መቀነሱን የቡና እና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።
Next articleካራማራ የኢትዮጵያዊነት ማኅተም።