
ባሕር ዳር፡ የካቲት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ115ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ ይከበራል፡፡ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ በዓሉን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በዓሉ”የ50 ዓመት የሴቶች ድምጽ ለእኩልነት እና ለበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ መልዕክት እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡ የበዓሉ መከበር ዋና ዓላማ በሴቶች ተሠርተው የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠል እና ችግሮችን በመፍታት የኢትዮጵያን ሴቶች ብልጽግና ማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡
ዕለቱን አስመለክቶ ግቦች ተጥለው ሥራዎች መሠራታቸውን አንስተዋል፡፡ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የዩኒቨርሲቲ እና ኮሌጆች ምሁራን ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እና በሴቶች የተሠሩ ውጤታማ ሥራዎች እንዲጎበኙ ማድረግ አንዱ ነው ብለዋል፡፡
ተጋላጭ የኾኑ ሴቶችን በገቢ ማስገኛ ሥራዎች ማሠማራት እና ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ ሴቶች ብቻ የሚሳተፉበት ባዛር በከተሞች ተዘጋጅቷል፡፡ ሴቶችን በልማት ኅብረት ማደራጀት እና ውጤታማ የኾኑትን ሞዴሎች ለሦሥተኛ ዙር ለማስመረቅ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል፡፡
ሴቶች በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካው ያመጡትን ውጤት በሚዲያ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ከመሥራት በተጨማሪ ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት የሴቶች ሚና ከፍተኛ በመኾኑ የፋይዳ መታወቂያ እንዲይዙ በንቅናቄ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡
ጤናማ እና ብቁ ሴቶችን ለመፍጠር ስፖርታዊ ውድድሮች እና የጡት እና የማኅጸን ካንሰር ቅድመ ምርመራ ሥራወች እንደተሠሩም ተናግረዋል፡፡
ተግባራቱ በሁሉም ዞኖች ሲከናወኑ ቆይተዋል ያሉት ኀላፊዋ የካቲት 27/2018 ዓ.ም በሁሉም ዞኖች የማጠቃለያ መርሐግብር ይካሄዳል ብለዋል፡፡ በጎንደር፣ ደሴ፣ ባሕር ዳር እና ደብረ ብርሃን ከተሞች የፌዴራል ከፍተኛ ሴት መሪዎች፣ በሌሎች በክልሉ ከተሞች ደግሞ የክልሉ ሴት መሪዎች ተገኝተው በሴቶች የተሠሩ ውጤታማ ሥራዎችን ይጎበኛሉ ብለዋል፡፡
የሴቶች ቀን ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሴቶች በመምረጥ እና በመመረጥ እንዲሳተፉ በቅንጅት የሚሠራበት እንደኾነም አመላክተዋል፡፡
በ50 ዓመት ውስጥ በሁሉም ዘርፎች ለውጦች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡ በማኅበራዊ ዘርፍ በትምህርት የሴቶች ተሳትፎ እና ውጤታማነት ከፍተኛ መኾኑን እና በጤናው ዘርፍ ለሴቶች የጤና አገልግሎት ተደራሽ እንዲኾን መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ በኢኮኖሚ ሴቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ኾነዋል፤ በፖለቲካው ዘርፍም የሴቶች ተሳትፎ መጨመሩን አንስተዋል፡፡
በሴቶች ጉዳይ የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሉን እና ውጤታማ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ከአዳራሽ ወጥቶ በውጤታማ ሴቶች መንደር እየተከበረ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
